አሜሪካ እና ታሊባን የመጀመሪያ ውይይታቸውን አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካ ባለስልጣናት ወታደሮቻቸውን ከአፍጋኒስታን ካስወጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍጋኒስታን ገዥ ታሊባን ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል።
በኳታር የተደረገው ውይይት ዋነኛ አንኳር ሃሳቦች አክራሪ ቡድኖችን መቆጣጠር ፣ የአሜሪካ ዜጎችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከአፍጋኒስታን ማስወጣት እና ሰብዓዊ ዕርዳታን ጨምሮ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው ሲሉ ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።
አሜሪካ ውይይቱን በተመለከተ ለታሊባን እውቅና የሚሰጥ አይደለም ብላለች።
ውይይቱ የተደረገው አፍጋኒስታን የከፋ የሚባለውን የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ካስተናገደች ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
በሰሜናዊ ኩንዱዝ ከተማ በሚገኝ መስጊድ ላይ በተፈጸመው የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ቢያንስ 50 ሰዎች ሲሞቱ ከ 100 በላይ ቆስለዋል።
ጥቃቱ የተፈፀመበት የሰይድ አባድ መስጊድ የሺዓ ሙስሊሞች ብበዛት የሚያዘወትሩት ሲሆን የተለያዩ ግዛቶችን የሚያስተዳድረው የእስልምና መንግሥት ቡድን ከጥቃቱ ጀርባ እጁ እንዳለ አስታውቋል።
የአፍጋኒስታኑ ታሊባን የሾመው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር ካን ሙታኪ ከአሜሪካ ጋር ያደረጉት ውይይትን አስመልክቶም ሁለቱ ወገኖች በ 2020 የተፈረመውን የዶሃ ስምምነት ውል ለማክበር መስማማታቸውን ተናግረዋል።
ይህ የዶሃ ስምምነት እንደ አልቃይዳ ያሉ ቡድኖች የአሜሪካን እና የአጋሮቿን ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይጥሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ሰፊ ግዴታዎችን በታሊባን ላይ ጥሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኩላቸው የአሜሪካ ባለስልጣናት ለታሊባን የኮቪድ ክትባቶችን እና የሰብአዊ ዕርዳታን ለማድረስ ድጋፍ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ገልጸዋል።
አሜሪካ በቅዳሜው ውይይቶች ዙሪያ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም ፣ ነገር ግን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቀደም ሲል ባለሥልጣናቱ ታሊባን የሴቶችን መብት እንዲያከብር ፣ ሁሉን ያካተተ መንግሥት እንዲመሰረት እና የሰብዓዊ ድርጅቶች እንዲሠሩ ለመፍቀድ ውይይቱን እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል።
ስብሰባው በዛሬው ዕለት እሁድ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
የአፍጋኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለጋዜጠኞች እንደገለፁት እስላማዊ ቡድኑ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት ማሻሻል ይፈልጋል ካሉ በኋላ ነገር ግን ማንም በማንም ሀገር የውስጥ ፖሊሲዎች ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ አስጠንቅቀዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ውይይቱ ከታሊባን ጋር በብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮች ላይ መቀጠሉን እንጂ ለቡድኑ ሕጋዊ ዕውቅና መስጠት አይደለም ብለዋል።
ውይይቱ በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ እየተካሄደ ባለበት ወቅት በአፍጋኒስታን የአርብ ጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓቶች እየተደረጉ ነበር።
"አስከሬኖቹን ሳንለያይ እየደራረብን እንቀብራለን ምንም አማራጭ ስለሌለን። እናም የጅምላ መቃብሮችን ማዘጋጀት አለብን" ብለዋል አንድ ሃዘንተኛ
የተባበሩት መንግስታት በበኩሉ የሰሞኑን ጥቃት "በዚህ ሳምንት በሃይማኖታዊ ተቋም ላይ ያነጣጠረ ሦስተኛ ገዳይ ጥቃት ነው። ይህ የሚያሰቅቅ የአመፅ ዘይቤ" አካል ነው ብሏል።












