ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና ውስጥ ጎርፍ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ አፈናቀለ
በቻይናዋ ሻንዢ ግዛት ውስጥ ባጋጠመ ከባድ የጎርፍ አደጋ ከ1.76 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ለጉዳት መዳረጉን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
ባለፈው ሳምንት ግዛቲቱ ውስጥ የጣለ ከባድ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት ሰበብ ከሰባ በላይ በሚሆኑ ወረዳዎችና ከተሞች ውስጥ ቤቶችን ፈርሰዋል።
እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ ሰዎችን ለማዳን የሚደረገውን ጥረት እያደናቀፈ መሆኑን ባለሥልጣንት ገልጸዋል።
አሁን የተከሰተው ጎርፍ ያጋጠመው ከሦስት ወራት በፊት ሄናን በተባለችው ግዛት ውስጥ የጣለ ከባድ ዝናብ ከ300 በላይ ሰዎችን ከገደለ በኋላ ነው።
ሄቤይ በተባለችው ግዛት ውስጥ አንድ አውቶቡስ ከሞላ ወንዝ ውስጥ ገብቶ የሦስት ሰዎች ህይወት አልፏል። በተጨማሪም ከ51 ተሳፋሪዎቹ መካከል 11ዱ የደረሱበት እንዳልታወቀ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የቻይና ሜትዮሮሎጂካል አስተዳደር እንዳለው ሻንዢ ውስጥ የደረሰውን የጎርፍ አደጋ ተከትሎ የሚደረገውን የነፍስ አድን ጥረትን እየጣለ ያለው የማያቋርጥ ዝናብና ወጀብ እያደናቀፈው መሆኑን አመልክቷል።
የበርካታ ጥንታዊ ሐውልቶች መገኛ በሆነችው ሻንዢ ውስጥ እየጣለ የሚገኘው ከባድ ዝናብ ለጉዳት ሊያጋልጣቸው እንደሚችል እየተነገረ ነው።
ዢንዋ የዜና ወኪል ባለሥልጣንትን ጠቅሶ እንደዘገበው ከ120,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በአስቸኳይ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ የተደረገ ሲሆን በግዛቲቱ ውስጥ 17,000 ቤቶች ፈርሰዋል።
ምንም እንኳን በአደጋው በሰዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት መረጃ ባይወጣም በመሬት መንሸራተት ሳቢያ አራት የፖሊስ መኮንኖች መሞታቸውን መንግሥታዊው ግሎባል ታይምስ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።
ከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅ ያጋጠማት የሻንዢ ግዛት ቻይና ውስጥ የድንጋይ ከሰል ከሚመረትባቸው ግዛቶች መካከል ዋነኛዋ ስትሆን፣ እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ ሳቢያ የማዕድን ማውጫዎችና የኬሚካል ፋብሪካዎች ሥራ እንዲያቆሙ ተገደዋል።
በኃይል መቋረጥ ሳቢያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት ቻይና ውስጥ ያጋጠመ ሲሆን፤ መንግሥት በወደቦችና በፋብሪካዎች የኤሌክትሪክ አጠቃቀም ላይ ላይ ገደብ እያደረገ ነው።
የግዛቲቱ አስተዳዳሪዎች 60 የድንጋይ ከሰል ማውጫዎች፣ 372 ሌሎች የማዕድን ማውጫዎች እና 14 አደገኛ ኬሚካል የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ሥራ እንዲያቆሙ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ብሎ ባለፈው ሳምንት 27 የድንጋይ ከሰል ማውጫዎች ሥራ እንዲያቆሙ ተደርገዋል።