ዋሊያዎቹ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ደቡብ አፍሪካን ዛሬ ይገጥማሉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት

የፎቶው ባለመብት, ISSOUF SANOGO

ታትሟል

በኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ከዚምባብዌ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሶስተኛ የምድብ ጨዋታውን ቅዳሜ መስከረም 28/2014 ዓ.ም በባህር ዳር ስቴዲየም ከባፋና ባፋናዎች ጋር ያደርጋል።

በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታው ወደ ጋና ያቀኑት ዋሊያዎቹ በጨዋታው አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት መሸነፋቸው የሚታወስ ነው። ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ኳስ ይዞ ለመጫወትና የበላይነት ለመውሰድ ቢሞክርም በጨዋታው ግን ግብ ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል።

ጨዋታው በተጀመረ 35ኛው ደቂቃ ላይ የጋናው ሚባራክ ዋክሶ ከርቀት የሞከራት ኳስ ወደ ግብነት ተቀይራ ጨዋታው በጋና አንድ ለባዶ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በመቀጠል በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በባህር ዳር ስቴዲየም ዚምባቡዌን የገጠመ ሲሆን ጨዋታውን አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ከባድ የተባለው ምድብ ውስጥ የተደለደሉት ዋሊያዎቹ ለድል ያበቃቻቸውን ግብ ማስቆጠር የቻሉት በጨዋታው መጠናቀቂያ ሰዓት ላይ የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ተከላካዩ አስቻለው ታመነ ወደ ግብነት በመቀየሩ ነው።

ጨዋታውን አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት በማሸነፍ ዋሊያዎቹ የመጀመሪያውን ሦስት ነጥብ በባህር ዳር ስታዲየም ማግኘት ችለዋል።

እስካሁን በምድቡ በተደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች ደቡብ አፍሪካ ዚምባብዌን ካሸነፈች በኋላ ከጋና ደግሞ አቻ ተለያይታለች። ዚምባብዌ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ አቻ ተለያይታ በኢትዮጵያ አንድ ለባዶ ተሸንፋለች።

በዚህም ምድቡን ደቡብ አፍሪካ በአራት ነጥብ ስትመራ፣ ጋናና ኢትዮጵያ በተመሳሳይ በሦስት ነጥብ በመያዝ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃቸውን አስጠብቀዋል። ዚምባቡዌ ደግሞ በአንድ ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ኳታር በምታስተናግደው የ2022 የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ እድላችን አሁንም ከፍተኛ ነው የሚሉት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ፤ ከደቡብ አፍሪካ አቻቸው ጋር ላለባቸው የምድብ ማጣሪያ በባህር ዳር በመከተም ዝግጅት ጀምረዋል።

ለዚህ ጨዋታ ዝግጅት ለማድረግ ደግሞ ለ25 ተጨዋቾች ጥሪ አድርገዋል።

በዚህም ግብ ጠባቂዎች ጀማል ጣሰው፣ ተክለማርያም ሻንቆና ፋሲል ገብረሚካኤል ሲሆኑ፤ ተከላካዮች አስቻለው ታመነ፣ አስራት ቱጂ፣ ሱሌማን ሀሚድ፣ ረመዳን የሱፍ፣ ያሬድ ባዬ፣ ደስታ ዮሐንስ፣ ምኞት ደበበና መናፍ አወል ተካተዋል።

አማካዮች ደግሞ ሽመልስ በቀለ ፣ ይሁኔ በላይ፣ ጋቶች ፓኖም፣ መሱድ መሐመድ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ታፈሰ ሠለሞን፣ ሽመክት ጉግሳና አማኑኤል ዮሐንስ ናቸው።

የፊት መስመር ተጫዋቾች ደግሞ አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ ጌታነህ ከበደ፣ አቤል ያለው፣ ቸርነት ጉግሳ፣ መስፍን ታፈሰና አቡበክር ናስር መሆናቸው ይፋ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በፌስቡክ ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት በአለም ዋንጫ ማጣሪያ የፊታችን ቅዳሜ የደቡብ አፍሪካ አቻውን የሚገጥሙት ዋልያዎቹ መደበኛ ልምምዳቸውን ሐሙስ ዕለት መስራታቸውን ገልጿል።

ለግብጹ ጎና ኤፍሲ የሚጫወተው የመሀል ክፍል አንቀሳቃሹ ሽምስ በቀለ ከቀናት በፊት ባህር ዳር የሚገኘውን ቡድን የተቀላቀለ ሲሆን ከቡድን አጋሮቹ ጋርም ልምምድ መስራቱን ፌደሬሽኑ አስታውቋል።