ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካዊው በ90ዎቹ መጨረሻ በፈጸመው ወንጀል በሞት ተቀጣ
አሜሪካ ሚዙሪ ውስጥ የሚገኝ አንድ ግለሰብ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1994 ላይ በፈጸመው የግድያ እና የዝርፊያ ወንጀል በሞት ተቀጣ።
ኧርነስት ጆንሰን የተባለው ግለሰብ አእምሯዊ የማመዛዘን ችግር አለበት ብለው ጠበቆች ቢከራከሩለትም ከሞት ቅጣት ግን ሊያስጥሉት አልቻሉም።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሞት ቅጣቱ ይዘግይ የሚለውን ሀሳብ ባለመቀበሉ ግለሰቡ ማክሰኞ ዕለት ገዳይ መርፌ ተወግቶ ሕይወቱ እንዲያልፍ ተደርጓል።
የ61 ዓመቱ ኧርነስት ምህረት ሊደረግልኝ ይገባል ብሎ መጠየቁን ተከትሎ የካቶሊኩ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ እና ሁለት የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት በሀሳቡ እንደሚስማሙ ገልጸው ነበር።
ኧርነስት እአአ 1994 ላይ በፈጸመው የዝርፊያ ወንጀል ወቅት ሦስት ሰዎችን ገድሏል።
የኧርነስት ጆንሰን ጠበቃ የሞት ፍርዱ እንዲቀልለት በተከራከሩበት ወቅት ግለሰቡ የአእምሮ ብቃት መፈተሻ ፈተናዎችን እንዲወስድ ሲደረግ የተገኘው ውጤት አእምሮው በደንብ እንዳልዳበረና የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ታዳጊ አእምሯዊ እድገት እንደበረው ተረጋግጧል ብለዋል።
የኧርነስት ጆንሰን ወላጅ እናት እርጉዝ በነበረችበት ወቅት ከፍተኛ የአልኮል መጠጥ ተጠቃሚ ስለነበረች ኧርነስት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ለአእምሮው መጎዳትም ይሄው እንደ ምክንያት ተጠቅሷል።
ከዚህ በተጨማሪም በአውሮፓውያኑ 2008 ጭንቅላቱ ውስጥ የነበረን እብጠት ለማስወገድ በተደረገለት ቀዶ ሕክምና ምክንያት አንድ የአንጎሉ ክፍል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።
ምንም እንኳን ጠበቆች ኧርነስት ካለበት የአእምሮ ችግር አንጻር እና በአውሮፓውያኑ 2002 በአሜሪካ ከጸደቀው የአአምእሮ ጉዳት ያለባቸው ሰዎችን የሚከለከላከለውን ሕግ በመጠቀስ በሞት መቀጣት እንደሌለበት ቢከራከሩም ፍርድ ቤቱ ግን ሳይቀበለው ቀርቷል።
ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን መከራከሪያ እንደማይቀበለውና ኧርነስት በሞት መቀጣት እንዳለበት እንደሚያምን አስታውቋል። የግዛቲቱ አስተዳዳሪም ቢሆኑ የሞት ፍርዱን ከማገድ ተቆጥበዋል ተብሏል።
የፖፕ ፍራንሲስ ተወካይ በበኩላቸው ጳጳሱ ለግዛቲቱ አስተዳዳሪ በጻፉት ደብዳቤ ለግለሰቡ ምህረት እንዲደረግለት መጠየቃቸውን ገልጸዋል።
ነገር ግን ሰኞ ዕለት አስተዳዳሪው ማይክ ፓርሰን የግዛቲቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኧርነስት ጆንሰን በፈጸመው ወንጀል ምክንያት የሞት ፍርድ ማስተላለፉን ገልጸው ፍርዱም ተፈጻሚ እንደሚሆን አስታውቀዋል።
ኧርነስት ጆንሰን ከመሞቱ በፊት ቢያንስ በጥይት ተተኩሶበት እንዲገደል ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል። በዚህም ምክንያት መርዛማ መርፌ ተወግቶ ሕይወቱ እንዲያልፍ ተርጓል።
ኧርነስት በእስር ላይ እያለ በጻፈው ደብዳቤ ደግሞ በፈጸመው ወንጀል መጸጸቱን በመግለጽ ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን ቤተሰቡን፣ ጓደኞቹን እንዲሁም ጠበቆቹን በሙሉ ላደረጉለት እርዳታ ምስጋናውን አቅርቧል።
ኧርነስት ጆንሰን በሚዙሪ ግዛት ውስጥ በሁለት ዓመት ውስጥ በፍርድ ቤት ውሳኔ የሞት ቅጣት የተፈጸመበት ሰባተኛው ሰው ነው።