ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሊባኖስ ከዓመት በኋላ ባለሀብቱን ፖለቲከኛ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጋ ሾመች
ሌባኖስ የቀድሞው አስተዳደር ሥልጣን ከለቀቀ በኋላ በአገሪቱ ቁጥር አንድ ባለሀብቱን ናጂብ ሚካቲን በጠቅላይ ሚኒስትርነት በመሰየም አዲስ መንግሥት አቋቋመች።
ከአንድ ዓመት በፊት ውድመትን ያስከተለው በቤይሩት ወደብ ላይ ከደረሰው ከባድ ፍንዳታ በኋላ ነበር የቀድሞው የሊባኖስ አስተዳር ሥልጣን የለቀቀው።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሊባኖስ ውስጥ ቀዳሚው ባለሀብት ሲሆኑ ከዚህ ቀደምም ሁለት ጊዜ በዚሁ ኃላፊነት ላይ አገልግለዋል።
ናጂብ ሚካቲ በጠቅላይ ሚኒስትር ቦታ ላይ መሰየምና ኢዲስ የካቢኔ ሚኒስትሮች መሾም የአገሪቱን ፖለቲካ እና አስተዳር ለወራት አሽመድምዶት የቆየውን ክፍተት ይሞላዋል ተብሏል።
አዲሱ መንግሥት የተቋቋመው ሊባኖስ በታሪኳ ከገጥሟት ቀውሶች የተወሳሰቡ የአገር ውስጥ በርካታ ችግሮችን እየታገለች ባለበት ጊዜ ነው።
የአገሪቱ ገንዘብ ዋጋ ወድቋል፣ የሥራ አጥ ቁጥርና የዋጋ ውድነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፣ የኤሌክትሪክ፣ የነዳጅ እና የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት ለሕዝቡን ኑሮ አክብዶታል።
በዚህ እየተነሳ መላዋ ሊባኖስ መሠረታዊ የፖለቲካ ለውጥ እንዲደረግ በሚጠይቁ የተቃውሞ ሰልፎች ስትናጥ እነሆ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት የቤይሩት ወደብን ያወደመውና ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን አሰቃቂ ፍንዳታ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሰን ዲያብ ሥልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ ሊባኖስ በአግባቡ ሥራውን የሚያከናውን መንግሥት ሳይኖራት ቆይታለች።
በወደቡ ላይ ፍንዳታ የተከሰተው በአግባቡ ባልተከማቸ አሞኒየም ናይትሬት በተባለ አደገኛ ንጥረ ነገር ሲሆን፤ አደጋው ለ203 ሰዎች ሞት ምክንያት ሲሆን ከ6ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
ፍንዳታው በቢሊዮኖች ዶላር የሚገመት የንበረት ውድመትን በአገሪቱ ላይ አስከትሏል።
በኮሮናቫይረስ ምክንያት በተከሰተ የኢኮኖሚ ቀውስ ወቅት የደረሰው ይህ አደጋ በሊባኖስ መንግሥት ላይ ከባድ ቁጣና ተቃውሞን ቀስቅሷል።
ተቃዋሚዎች የፍንዳታውን ምክንያት በአገሪቱ መንግሥት ውስጥ ያለው ሙስና፣ የብቃት ማነስና ብልሹ ፖለቲካዊ ሹመት እንደሆነ ከሰዋል።
አደጋው አገሪቱ የገጠማትን ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ቀውስ የበለጠ ያባባሰው ሲሆን ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ የሊባኖስ ገንዘብ 90 በመቶ የመግዛት አቅሙን አጥቷል። በዚህም ሳቢያ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች በድህነት ውስጥ ለመኖር ተገደዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሾሙ በኋላ ናጂብ ሚካቲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቀዳሚ ተግባራቸው የአገሪቱን ኢኮኖሚ መታደግ መሆኑን አመልክተው ለዚህም ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ጋር ንግግር እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።
ባለጸጋው አዲሱ የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምረውም ምንም እንኳን እርሳቸው ሀብታም ቢሆኑም በአገሪቱ ያለው ቀውስ በሕዝቡ ህይወት ላይ ምን ያህል ጫናን እንዳሳረፈ እንደሚረዱ ገልጸል።
በሊባኖስ ያለው ሐይማኖትን መሠረት ያደረገ የሥልጣን ክፍፍል ከአንድ ዓመት በፊት ሐሰን ዲኣብ ሥልጣን ሲለቁ አዲስ ለመንግሥት ለመመስረት የተደረገውን ጥረት እንዳይሳካ አድርጎት ቆይቷል።
እንደ አውሮፓውያኑ ከ1975 አስከ 1990 በአገሪቱ የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ የተዘረጋው ሥርዓት የፖለቲካ ሥልጣን በተለያዩ የሐይማኖት ተከታዮች እንዲያዝ ያደርጋል።
በዚህም መሠረት የአገሪቱ ፕሬዝዳንትነት ሥልጣን በክርስቲያኖች የሚያዝ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታው በሱኒ ሙስሊሞች እንዲሁም የምክር ቤት አፈ ጉባኤነት ቦታው ደግሞ በሺዓ ሙስሊሞች እንዲዝ ይደረጋል።
አሁን ተከስቶ አገሪቱን በአግባቡ የሚመራ አስተዳደር እንዳይኖራት ያደረገው ይህ ሂደት ጊዜን የሚፈለግና ውስብስብ ነው።
በዚህ አሰራር የሚሾሙት ሚኒስትሮች በሁሉም ሐይማኖቶችና አንጃዎች ይሁንታን ካላገኙ መንግሥት የመመስረቱ ሂደት ረጅም ጊዜን በሚፈጅ ድርድር ይጓተታል።