ፖላንድ ውስጥ መርዛማ እንጉዳይ የበላው አፍጋኒስታዊ ታዳጊ ሕይወቱ አለፈ

አፍጋናውያን ካቡል ውስጥ ወደ አውሮፕላን ሲገቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ታሊባን አገሪቱን ከተቇጣጠረ በኋላ ከአንድ ሺህ በላይ አፍጋኖች ወደ ፖላንድ ተወስደዋል
ታትሟል

የአምስት ዓመቱ አፍጋኒስታናዊ ታዳጊ ፖላንድ ውስጥ መርዛማ እንጉዳይ ከተመገበ በኋላ ሕይወቱ ማለፉ ተነገረ።

የአምስት ዓመቱ ታዳጊ ከሌሎች የቤተሰቡ አባላቱ ጋር ታሊባንን ሸሽተው ወደ ፖላንድ ከሄዱ በቀናት ልዩነት ውስጥ ነው እንጉዳዩን ከተመገበ በኋላ ሕይወቱ ያለፈው።

የታዳጊው የስድስት ዓመት ወንድም በተመሳሳይ መርዛማውን እንጉዳይ ከተመገበ በኋላ በጠና ታሞ እንደሚገኝ ሐኪሞች አስታውቀዋል።

ሁለቱ ታዳጊዎች ከአንድ ሳምንት በፊት ከወላጆቻቸው ጋር ከአፍጋኒስታን ከወጡ በኋላ ከፖላንድ መዲና ዋርሶው በቅርብ እርቀት ላይ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ይገኙ ነበር።

የቤተሰብ አባላቱ ከመጠለያ ጣቢያው በቅርብ እርቀት ከሚገኝ ጫካ ውስጥ እንጉዳዩን ቆርጠው በሾርባ መልክ መመገባቸው በስፋት ተዘግቧል።

መገናኛ ብዙኃን ታዳጊዎቹ እንጉዳዩን የተመገቡት በቂ የምግብ አቅርቦት ባለማግኘታቸው ነው ሲሉ ዘግበዋል። የፖላንድ ባለስልጣናት ግን በቂ ምግብ እየቀረበ ነው በማለት ዘገባውን ውድቅ አድርገዋል።

ታዳጊዎቹ እንጉዳዩን ከተመገቡ በቀጣዩ ቀን ነው ወደ ሆስፒታል የተወሰዱት።

"ያለመታደል ሆኖ ልጆቹን ልንረዳቸው አንችልም" በማለት የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ማሬክ ሚግዳል ተናግረዋል። ሐኪሙ አምስት ዓመቱ ታዳጊ ሕይወቱ ማለፉንም አረጋግጠዋል።

በሕይወት የሚገኘው ሌላኛው ታዳጊ ከሞት የተረፈው የጉበት ነቅለ ተከላ ከተካሄደለት በኋላ መሆኑን ሐኪሙ ተናግረው፣ የአምስት ዓመቱ ታዳጊ ግን ከፍተኛ የሆኑ የአእምሮ ጉዳት አጋጥሞት ስለነበረ ቀዶ ህክምናውን ማድረግ አለመቻሉን ዶ/ር ሚግዳል ተናግረዋል።

ሌላ እንጉዳዩን የተመገበች የ17 ዓመት ሴት ወጣት በተመሳሳይ ሆስፒታል ሕክምና ተደርጎላት መውጣቷ ተገልጿል።

የታዳጊዎቹ የቤተሰብ አባላት እንዴት ሊመረዙ እንደቻሉ ምርመራ መጀመሩን ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።

የፖላንድ የውጭ አገር ዜጎች ጉዳይ ቢሮ ቃል አቀባይ ከአፍጋኒስታን ወደ ፖላንድ የተወሰዱ ሰዎች በቀን ሦስት ጊዜ ምግብ እየቀረበላቸው ነው ብለዋል።

የአፍጋኒስታን ዜጎች በዱር የሚበቅሉ እንጉዳዮችን እንዳይመገቡ ተነግሯቸዋል ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ከኔቶ ኃይል ጋር አብራ አፍጋኒስታን ውስጥ ስትሰራ የነበረችው ፖላንድ 1000 የአፍጋኒስታን ዜጎችን ከአፍጋኒስታን አስወጥታ ተቀብላለች።

ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ በፖላንድ የሚቆዩ ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ወደ ሌላ ሦስተኛ አገር ይሸጋገራሉ ተብሏል።

የፖላንድ መንግሥት በአገሪቱ ለህልፈት ሊያደርሱ የሚችሉ ከ250 በላይ የተክል አይነቶች መኖራቸውን ይገልጻል።