አፍጋኒስታን፡ የታሊባንን ህልውና ያስቀጠሉት ኳታር እና ቱርክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ምዕራባውያን በዚህ ሳምንት አፍጋኒስታንን ለቀው ሲወጡ ታሊባኖች ደስታቸውን ለማብሰር ካቡልን በተኩስ አናውጠዋታል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአፍጋን ዜጎች ከፊታቸው ውሉ ያልለየ ህይወት ይጠብቃቸዋል።
ታሊባንም ቢሆን የአስተዳደር ዘዴው ከመላው ዓለም ሊያቆራርጠው ይችላል።
የአገሪቱ እስላማዊ ገዥዎች ወደ ስልጣን መመለሳቸውን ተከትሎ የዓለም ሃገራት ተጽዕኗቸውን ለማሳደር እየተፍጨረጨሩ ነው። በዚህ ሂደት ከአረብ እና ከሙስሊሙ ዓለም የመጡ ሁለት ሃገራት አስታራቂ እና አስተባባሪ በመሆን ቁልፍ ሚና ይዘው ብቅ ብለዋል- ኳታር እና ቱርክ።
ሁለቱም ሃገራት በቅርቡ ከታሊባን ጋር ያላቸውን ወዳጅነት እያጎለበቱት ነው። የሁለቱም ዓይን ዕድሎችን እያየ ነው። ይህም በመካከለኛው ምስራቅ የከረመውን ተቀናቃኝነት ሊያቀጣጥል ይችላል።
ቱርክ እና ኳታር ለቀጠናው እስላማዊ እንቅስቃሴ ቅርብ ሲሆኑ እንደ ግብጽ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ካሉ ኃይሎች ጋር ብዙ ጊዜ ውጥረት ውስጥ ይገባሉ።
እነዚህ ሃገራት እንደነዚህ ያሉ እንቅስቃሴዎችን እንደ ህልውና ስጋት ስለሚመለከቱ ነው ።
የታሊባን ወደ ስልጣን መመለስ በእስልምና ሕግ መሠረት መንግስትን እና ህብረተሰብን እንደገና ለማዘዝ የሚፈልግ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምን እንደገና ማምጣት ነው። ለጊዜው ግን ይህ በደቡብ እስያ ያለ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከታሊባን ጋር ንግግር
በ1990ዎቹ ታሊባን ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ከእነሱ ጋር መደበኛ ግንኙነት የነበራቸው ሦስት ሃገሮች ብቻ ነበሩ ። እነሱም ፓኪስታን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ናቸው።
ኋለኞቹ ሁለቱ ሃገሮች መስከረም 11/2001 በአሜሪካ ከተፈጸሙ ጥቃቶች በኋላ ሁሉንም ኦፊሴላዊ ግንኙነቶች አቋርጠዋል። ሆኖም ከሳዑዲ ግለሰቦች የገንዘብ ድጋፍ በድብቅ ለዓመታት መቀጠሉ ተዘገቧል።
የሳዑዲ ባለሥልጣናት ቀደም ሲል ለታሊባኖች ኦፊሴላዊ የገንዘብ ድጋፍ የለም ብለው የካዱ ሲሆን የግል የገንዘብ ድጋፍን ለማስቆም ጠንካራ እርምጃዎች አሉ ብለዋል።
የአሜሪካ ወታደሮች በአፍጋኒስታን መገኘታቸው በአሜሪካውያን ዘንድ አለመወደዱ ሲጨምር የዲፕሎማሲ ሥራ ለመሥራት ለሚችሉ ሃገሮች በሩ ተከፈተ።
ኳታር እና ቱርክ ከታሊባን ጋር ለመገናኘት የተለያዩ መንገዶችን መርጠዋል።
የፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ጦርነቱን ለማቆም መጣሩን ተከትሎ ኳታር እአአ ከ 2011 ጀምሮ የሠላም ጥረቶች ለመወያየት የታሊባን መሪዎችን አስተናግዳለች።
አወዛጋቢ ሂደት ነበር። በአብረቅራቂው የዶሃ ከተማ ዳርቻ ላይ የታሊባን ባንዲራ ማየቱ ብዙዎችን አስቆጥቷል።
ለኳታሮች በኢራን እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል ለምትቀመጥ ሃገር ወሳኝ የውጭ ፖሊሲን ለመተግበር ለሦስት አስርት ዓመታት የዘለቀ ምኞትን እንዲያዳብር ረድቷል።
በአፍጋኒስታን ጠንካራ ታሪካዊ እና የጎሳ ትስስር ያላት ቱርክ እንደ ኔቶ ህብረት አባልነቷ ተዋጊ ባልሆኑ ልዑኮቿ ተሳታፊ ሆና ቆይታለች።
እንደ ተንታኞች ገለጻ ይህ አጋጣሚ ከአንዳንድ የታሊባን ጋር ግንኙነት ካላቸው ሚሊሻዎች ጋር የጠበቀ የስለላ ግንኙነት እንደትፈጥር ረድቷታል። ቱርክ በተጨማሪም ታሊባኖች መጀመሪያ ከመጡበት ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች መገኛ ፓኪስታን ጋርም አጋር ናት።
የካቡል አየር ማረፊያ ውጥረት ውስጥ በነበረበት ረቡዕ ዕለት የቱርክ ባለሥልጣናት ከታሊባን ጋር ለሦስት ሰዓታት ያህል ውይይት አድርገዋል። ከውይይቶቹ አንዱ የቱርክ ወታደሮች ለስድስት ዓመታት ሲጠብቁት ስለነበረው የአውሮፕላን ማረፊያው የወደፊት አሠራር ነበር። የአፍጋኒስታንን "ወረራ" ለማጠናቀቅ የቱርክ ወታደሮች ከሌሎች የውጭ ኃይሎች ጋር እንዲወጡ ታሊባን አጥብቆ ጠይቆ ነበር። ያለፈው ሳምንት ስብሰባ ግን የሰፊው አጀንዳ አካል መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ከታሊባን መሪዎች የተላኩ መልዕክቶችን "ጥንቃቄ በተሞላበት ብሩህ ተስፋ" መመልከታቸውን ገልጸዋል። ከቡድኑ ጋር ስላለው ግንኙነት ትችት ሲጠየቁም ከማን ጋር እንደሚነጋገሩ "ከማንም ፈቃድ አላገኝም" ብለዋል።
"ይህ ዲፕሎማሲ ነው" ብለዋል በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት።
አክለውም "ቱርክ ለአፍጋኒስታን አንድነት ሁሉንም ዓይነት ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ ነች። ሆኖም ጥንቃቄ የተሞላበትን መንገድን ትከተላለች" ብለዋል።
ካቡልን ከተቆጣጠሩ ጀምሮ በተለይ በዶሃ በኩል ብዙ ሃገሮች ከታሊባን ጋር አንድ ዓይነት ግንኙነት ለማቆየት ሞክረዋል። ምንም እንኳን በስጋት የተሞላ ቢሆንም ቱርክ ግን መሬት ላይ ትስስር ለማዳበር ጠንካራ መሠረት ካላቸው መካከል ናት።
ኳታርን በተመለከተ የሽምግልና ሚናዋ የባህረ ሰላጤውን የዓመታት ብጥብጥ ከማባባስ ይልቅ እንደሚቀንሰው ባለሥልጣናት ተስፋ ያደርጋሉ።
ዶሃ የበርካታ የመካከለኛው ምስራቅ ታላላቅ ግጭቶች ተፎካካሪ ቡድኖች ድርድርን መርታለች። የአረብ አብዮትን ተከትሎ ግን የባህረ ሰላጤው ተፎካካሪዎቿ ለአክራሪ እስልሚስቶች ወግናለች ሲሉ ይከሳሉ።
እአአ 2017 ላይ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ግብፅ እና ባህሬን ከኢራን ጋር በጣም ቅርብ መሆኗን በመጥቀስ እና በመንግስት ባለቤትነት ስር ባለው የዜና ጣቢያዋ አልጀዚራ በኩል አለመረጋጋትን አባብሳለች ሲሉ ግንኙነታቸውን አቋርጠዋል። ኳታር ግን ውድቅ አድርጋዋለች። በኋላ ግን ግነኙነቱ ተመልሷል።
ለአፍጋኒስታን ዜጎች መጻኢው ዕድል ምን እንደያዘ ባልታወቀበት በአሁኑ ጊዜ ኳታር እና ቱርክ ከውጭው ዓለም ከታሊባን ጋር ከሚነጋገሩት መካከል ናቸው። ለወደፊቱ ቻይና እና ሩሲያም በካቡል ግንኙነት ላይ ይወዳደራሉ።
የታሊባን ወደ መንበሩ መመለሱ ያነሳቻው መዘዞች ገና መጀመራቸው ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተራ የአፍጋን ዜጎች ሕይወት ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን አሁን ላይ መገመት አስቸጋሪ ይሆናል።












