ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ዓለም አቀፍ የግብ ክብረ ወሰንን ሰበረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ36 ዓመቱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ አሁንም በዓለም እግር ኳስ መድረክ ታሪክ መስራቱን ቀጥሏል።
ሮናልዶ ትናንት ምሽት አገሩ ፖርቹጋል በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከአየርላንድ ባደረገችው ጨዋታ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር በወንዶች ዓለም አቀፍ ውድድር ከፍተኛውን ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች መሆን ችሏል።
ፖርቹጋል አየርላንድን 2 ለ1 ባሸነፈችበት ጨዋታ ሮናልዶ መጀመሪያ ላይ የተገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ወደ ግብ መቀየር አለመቻሉ በርካቶችን ያስቆጨ ቢሆንም በጨዋታው መገባደጃ አካባቢ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች በዓለማችን ለብሄራዊ ቡድን ከፍተኛ ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ሆኗል።
በዚህም መሰረት ሮናልዶ ለአገሩ 111 ግቦችን በስሙ ያስቆጠረ ሲሆን ከዚህ በፊት ሪከርዱን ይዞት የቆየው ኢራናዊው አሊ ዳኢ ነበር። እሱም ከአውሮፓውያኑ 1993 እስከ 2006 ባሉት ዓመታት ባደረጋቸው ጨዋታዎች 109 ግቦችን አስቆጥሮ ነበር።
ሮናልዶ በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ፈረንሳይ ላይ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች አማካይነት የአሊን ክብረ ወሰን መጋራት ችሎ የነበረ ሲሆን በርካቶችም ይህ ዓመት ሳይጠናቀቅ ተጨማሪ ጎሎችን እንደሚያስቆጥርና ክብረ ወሰኑን የግሉ እንደሚያደርገው ሲገልጹ ነበር።
ከዚህ ክብረ ወሰን በተጨማሪ ደግሞ፤ ባሳለፍነው ሳምንት ለማንቸስተር ዩናይትድ በድጋሚ የፈረመው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ለብሄራዊ ቡድን 180 ጊዜ ጨዋታዎችን በማድረግ በአውሮፓ ለብሄራዊ ቡድን በመጫወት አሁንም ክብረ ወሰኑን ከስፔኑ ሰርጂዮ ራሞስ ጋር መጋራት ችሏል።
በዓለማችን እግር ኳስ ታሪክ ለብሄራዊ ቡድን ከፍተኛውን ጨዋታ በማድረግ ክብረ ወሰኑን የያዘው ደግሞ ማሌዢያዊው ሶህ ቺን አን ሲሆን ለአገሩም ከአውሮፓውያኑ 1969 እስከ 1984 ባሉት ዓመታት 195 ጊዜ ተጫውቷል።
ከጁቬንቱስ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ዝውውሩን የጨረሰው ሮናልዶ ለብሄራዊ ቡድን ከ90 በላይ ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ሁለተኛው ተጫዋች ሲሆን አንደኛው ደግሞ ኢራናዊው አሊ ነው።
''በጣም ደስተኛ ነኝ። ክብረ ወሰኑን በመስበሬ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን በጨዋታው መጨረሻ አካባቢ የተለየ እንቅስቃሴ አድርገናል። ባለቀ ሰአት ለአገሬ ሁለት ግብ ማስቆጠሬም ጥሩ ነው። የብድን አጋሮቼም በጣም የሚደነቁ ነበሩ። እስከመጨረሻው ድረስ ተስፋ አልቆረጥንም ነበር። በጣም ደስ ብሎኛል'' ሲል ደስታውን ገልጿል ሮናልዶ።
በበርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪያን የዓለማችን የምን ጊዜም ምርጥ ተጫዋች እየተባለ የሚሞካሸው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ይህን ታሪክ መስራቱ ይበልጥ ይህ ክብር ይገባዋል ለሚሉት ትልቅ ማሳያ ሆኗል።
ሮናልዶ ለበርካታ ዓመታት ከፖርቹጋል እስከ እንግሊዝ እንዲሁም ከስፔን እስከ ጣልያን በዘለቀው አስገራሚ የእግር ኳስ ህይወቱ በቻምፒየንስ ሊግ ከፍተኛውን ግብ ማስቆጠር የቻለ ተጫዋች ሲሆን እስካሁንም 5 ጊዜ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ ነው።
በጣም በሚያስገርም ሁኔታ ደግሞ ሮናልዶ ካስቆጠራቸው ግቦች መካከል ግማሽ የሚሆኑትን ያስቆጠረው በጨዋታዎች የመጨረሻ 30 ደቂቃዎች ውስጥ ነው። 33 ግቦችን ደግሞ በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች አስቆጥሯል።
ሮናልዶ እስካሁን ባደረጋቸው 180 ጨዋታዎች ለአገሩ 11 ግቦችን ሲያስቆጥር በርካቶች ከሮናልዶ በላይ ነው እያሉ የሚያሞካሹት አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ ደግሞ በ151 ጨዋታዎች 76 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ከዚህ በኋላ ደግሞ የ34 ዓመቱ ሜሲ ይህንን የሮናልዶ ክብረ ወሰን የማሻሻል እድሉ ያለው አይመስልም።












