ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
600 ሚሊየን ዶላር የዘረፈው ግለሰብ ገንዘቡን ለባለቤቱ መለሰ
600 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ክሪፕቶከረንሲ የዘረፈው የኮምፒውተር ጠላፊ አብዛኛውን ገንዘብ ለባለቤቱ መመለሱ ተሰምቷል።
ዕለተ ሐሙስ ነው ፖሊ ኔትዎርክ የተሰኘው ተቋም 268 ሚሊየን ዶላር የሚሆን ኢተር የተሰኘው ክሪፕቶከረንሲ መመለሱን በትዊተር ገፁ ይፋ ያደረገው።
ባለፉት 24 ሰዓታት ደግሞ ጠላፊው 342 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ክሪፕቶከረንሲ መመለሱ ተሰምቷል።
ኮምፒውተር ጠልፎ መረጃ ከመዘበረ በኋላ ከድርጅቶቹ ካሳ የሚጠይቀው ግለሰብ ለምን ፖሊ ኔትዎርክ የተባለውን ድርጅት እንደዘረፈና የቀረበለትን ካሳ ይፋ አድርጓል።
ኩባንያው ጠላፊው 600 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣውን ክሪፕቶከረንሲ ከመለሰ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰጠው ቃል መግባቱ ተሰምቷል።
ይህ ጉዳይ የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎችን ስጋት ላይ ጥሏል።
ነገር ግን ጠላፊው ድርጅቱ ያቀረበለትን ግማሽ ሚሊየን ዶላር እንደማይፈልግ ተናግሯል።
ድርጅቱ ሐሙስ ዕለት አብዛኛው ክሪፕቶከረንሲ ቢመለስም የተወሰነ ገንዘብ እንደሚቀር በትዊተር ገፁ ይፋ አድርጓል።
"ጠላፊው አሁን እጁ ላይ 33.4 ሚሊየን ዶላር ይገኛል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ቴዘር የተሰኘው ክሪፕቶከረንሲ ዝውውሩን በማገዱ ነው" ሲሉ ለንደን የሚገኙት የክሪፕቶከረንሲ ተንታኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጠላፊው እጅ ላይ የሚገኘው ገንዘብ የሚመለስ ይሁን አሊያም ድርጅቱ ለጠላፊው የሰጠው ካሳ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
ፖሊ ኔትዎርክ ከገንዘብ ቋቱ ረብጣ ገንዘብ እንደተዘረፈበት ይፋ ያደረገው ባለፈው ማክሰኞ ነበር።
ከዝርፊያው በኋላ ድርጅቱ ዘራፊዎቹ እንዲያገኙትና የዘረፉትን ገንዘብ እንዲመልሱ የሚያሳስብ ጽሑፍ ትዊተር ገፁ ላይ አስፍሮ ነበር።
ማንነቱ ያልታወቀው ጠላፊ ድርጅቱን የዘረፈው እንዲሁ ለመዝናናት ሲልና ፖሊ ኔትዎርክ የተሰኘው ተቋም ጥበቃውን እንዲያጠናክር እንደሆነ ተናግሯል።
ምንም እንኳ የጠላፊው ማንነት አይታወቅ እንጂ ድርጅቱ 'ሚስተር ዋይት ሃርት' ሲል እየጠራው ነው።
ዋይት ሃርት የተሰኙ የኮምፒውተር ጠላፊዎች ብዙ ጊዜ ኮምፒውተር ጠልፈው ድርጅቶች ደህንነታቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያሳስቡ ናቸው።
ድርጅቱ ለጠላፊው ግማሽ ሚሊየን ዶላርና ካሳ 'የአንከስህም ቃል' መግባታቸው ሌሎች ጠላፊዎችን ያበረታታል ሲሉ የሳይበር ደህንነት ሰዎች ስጋታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ።