አትሌት ሲፋን ሐሰን ለኢትዮጵያ ባለመሮጤ ፀፀት አይሰማኝም አለች

ቃልኪዳን፣ ሲፋንና ለተሰንበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በቶኪዮ ኦሎምፒክ የሜዳሊያ "ሦስታ" በመሥራት ዓለምን ያስደነቀችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ ሯጭ ሲፋን ሐሰን ኢትዮጵያን ወክላ ባለመሮጧ አንዳችም ፀፀት እንደማይሰማት ተናገረች፡፡

አትሌት ሲፋን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጦርነት አገሪቱን ድምጥማጧን እያጠፋት ነው ብላለች፡፡

በፖለቲካ ሥልጣን መጋራት የተሻለ ሁኔታ ሊያመጣ እንደሚችልና ይህም ሌሎች በርካታ ሯጮች ወደፊት ለሌሎች አገሮች መሮጥ ትተው ለኢትዮጵያ እንዲሮጡ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁማለች፡፡

አትሌት ሲፋን ለኔዘርላንድስ በ5ሺህ እና በ10ሺህ ወርቅ አስገኝታለች፡፡ በ1ሺ 500 ደግሞ ነሐስ አግኝታለች፡፡

አትሌት ሲፋን ከኢትዮጵያ ወደ ኔዘርላንድስ የወጣችው ገና በ14 ዓመቷ ነበር፡፡

የ28 ዓመቷ ሲፋን በኦሮሚያ ክልል ነው ያደገችው፡፡ በወቅቱ የራስ ገዝ ጥያቄ ይነሳ የነበረበት ሲሆን ለነጻነት የሚዋጉ ኃይሎች ጥቃት ይፈጽሙ ነበር ብላለች፡፡

ሲፋን በ10ሺህ ሜትር ያሸነፈቻት በርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ያላትን ኢትዮጵያዊቷን ለተሰንበት ግደይን ጭምር በመምራት ነው፡፡

ለተሰንበት የተገኘችው ደግሞ አሁን በጦርነት እየታመሰች ከምትገኘው ትግራይ ነው፡፡

ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ሐሳቧን የሰጠችው ሲፋን ሐሰን ያን ወቅት በኦሮሚያ የነበረው የሰዎች ግድያ ልብ የሚሰብር እንደነበር አስታውሳለች፡፡

‹‹ከዚያች አገር በመሰደዴ አንዳች ቅሬታ የለኝም፡፡ መመለስም አልፈልግም፡፡ ማሰቡ ራሱ ያመኛል፡፡›› ብላለች፡፡

ሲፋን በፈረንጆቹ እስከ 2007 ደስ የሚል የልጅነት ጊዜ እንዳሳለፈችና ከዚያ በኋላ ግን በኦሮሚያ በነበረው ውጊያ ነገሮች እየተበላሹ መምጣታቸውን አስታውሳለች፡፡

በቶኪዮ የ10ሺህ ሜትር የሜዳሊያ አሸናፊዎች ሥነ ሥርዓት መድረኩ በትውልደ ኢትዮጵያዊያን ነበር የተሞላው፡፡ሆኖም ለተሰንበት ብቻ ናት ኢትዮጵያን የወከለችው፡፡

የብር ሜዳሊያ ያገኘችው ቃልኪዳን ገዛኸኝ ባህሬንን ትወክል እንጂ ትውልደ ኢትዮጵያዊት ናት፡፡

በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በብሔር ግጭት ውጥረት ስሟ የሚነሳ ሲሆን ይህ ሁኔታ አገሪቱ በርካታ አትሌቶችን እንድታጣ ምክንያት ሆኗል ብላለች ሲፋን ሐሰን፡፡

‹‹ትዝ ይለኛል በፊት ወጣቱ እርስ በእርስ ይዋደድ ነበር፡፡ አሁን ግን እርስ በእርሱ የሚጠላላ ሆኗል፡፡ በፊት ሁሉም ራሱን ኢትዮጵያዊ ብሎ ይጠራ ነበር፡፡ አሁን ግን እርግጠኛ ነኝ ብዙ ትግራዊያን ራሳቸውን ኢትዮጵያዊ ብለው አይጠሩም›› ብላለች ሲፋን፡፡

በሰኔ ወር ለተሰንበት በ10ሺህ ሜትር ሁለት ቀናት ብቻ የቆየውን የሲፋንን የዓለም ክብረ ወሰን በርቀቱ ስትወስድ በርካታ የስፖርት ወዳጆች ወደ ዓለም አቀፉ የትሌቲክስ ማኅበር ማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ በመሄድ ክብረ ወሰኑ የትግራዋይት እንጂ የኢትዮጵያ አይደለም ሲሉ ይጽፉ ነበር፡፡

በዚህ ወር መጀመርያ የተባበሩት መንግሥታት አፋጣኝ የሰብአዊ እርዳታ በኦሮሚያ እንደሚያስፈልግ የጠቀሰ ሲሆን በትግራይ ደግሞ አራት ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ እርዳታን ይሻሉ ሲሉ መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡

‹‹ለተሰንበት ድንቅ አትሌት ናት፡፡ የመጣችበት ቦታ ግን ሕጻናት ይደፈራሉ፤ አስቀያሚ ሁኔታ ነው ያለው፤ ያሳዝናል›› ብላለች ሲፋን ለቢቢሲ፡፡

"አስበሽዋል! ልክ እንደኔው ሕልም የነበራቸው ስንትና ስንት ሴቶች እንደተደፈሩ?" ስትል ሁኔታውን ምን ያህል እንደሚያውክ አብራርታለች፡፡

ከኦሮሚያ የተገኙት የአሁን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ተቺዎች ለክልሎች የራስ ገዝ አስተዳደርን ከመስጠት ይልቅ ማዕከላዊ መንግሥትን አጠናክሮ አሀዳዊ መንግሥት ለመፍጠር ይሞክራሉ ሲሉ ይወቅሷቸዋል፡፡

‹‹እኔ እሱን ብሆን ዘወር እል ነበር፡፡ ሥልጣኑን ለሕዝቦች እሰጥ ነበር፣ የሚፈልጉትን እንደሚርጡ አደርግ ነበር፡፡›› ብላለች ሲፋን ሐሰን፡፡