ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሱዳን የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤትን ለመቀላቀል የቀረበውን ረቂቅ አጸደቀች
የሱዳን የሽግግር ካቢኔ አገሪቱ የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤትን (አይሲሲ) እንድትቀላለቀል የሚያስችለውን ረቂቅ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።
ረቂቅ አዋጁ የጸደቀው በስልጣን ላይ ያለው የአስተዳደር ካውንስል እና ካቢኔው ህጉን ከማጽደቃቸው በፊት እንደ ዝግጅት መሆኑም ተገልጿል።
''ፍትህ እና ተጠያቂነት የሱዳን የጀርባ አጥንት ናቸው፤ለየሕግ የበላይነት ቁርጠኛና አገሪቱን ለመገንባት ለምናደርገው ስራ ወሳኝ ነው'' ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ይህ ማለት ደግሞ ሱዳን የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት በምዕራባዊ ዳርፉር ግዛት ተፈጽመዋል በተባሉ የጦር ወንጀልና የዘር ማጥፋት የሚጠረጠሩ መሪዎችና ኃላፊዎች አሳልፋ እንድትሰጥ ሊያደርጋት የሚያስችል ሲሆን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽርም ይገኙበታል።
ግንቦት ወር ላይ የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት በአውሮፓውያኑ ከ2003 እስከ 2004 ዳርፉር ውስጥ ከፍተኛ የሰብአዊ ወንጀል የሚጠረጠሩት የአሊ ኩሻይብ ሙሉ የክስ መዝገብ ሰምቷል።
ከነሃሴ 2019 በኋላ ሱዳን በጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ስትመራ የቆየች ሲሆን የሽግግር መንግሥቱም የቀድሞው ፕሬዝዳንት አስተዳደር ወቅት በዳርፉር ለተፈጸሙ ወንጀሎች ተጎጂዎች ፍትህ እንደሚያስገኝ ቃል ገብቷል።
በያዝነው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ደግሞ የሱዳን አቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት የአገሪቱ የቀድሞው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት አሊ ካርቲ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲጋዙ ትዕዛዝ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው።
ከ30 ዓመት በፊት በፈረንጆቹ በ1989 ኦማር አልበሽር በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ስልጣን ሲመጡ ሁነኛ የመፈንቅለ መንግሥቱ አቀናባሪ ነበሩ ተብለው ነው አሊ ካርት የእስር ትዕዛዝ የተላለፈባቸው።
አሊ ካርት ባለፉት ዓመታትም በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በብዛት ሲወቀሱ ቆይተዋል።
በተለይ በ1990ዎቹ እርሳቸው የመንግሥት ሹም ሆነው በደቡብ ሱዳን ለሚሊሻዎች ትዕዛዝ በመስጠት ከፍተኛ ጭፍጨፋ አስደርገዋል በማለት ይከሷቸዋል።
በዳርፉር በታጣቂዎችና በሱዳን መንግሥት ደጋፊ ጦሮች መካከል ውጊያ የተጀመረው በጎርጎሳውያኑ 2003 ነበር። እንደተባበሩት መንግሥታት ከሆነ በዚህ ግጭት 300ሺህ ሰዎች ሞተዋል።