ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢዜማ በ28 ምርጫ ወረዳዎች ምርጫ እንዲደገም ያቀረበው አቤቱታ ላይ ቦርዱ ምላሽ እንዲሰጥ ፍርድ ቤት ወሰነ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሰኔ 14 በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ በሃያ ስምንት የምርጫ ወረዳዎች ምርጫው እንዲደደገም ያቀረበው አቤቱታ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምላሽ እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል።
ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ የምርጫ ጉዳይ ችሎት በዛሬው ዕለት መሆኑንም ኢዜማ በማህበራዊ ትስስር ገፁ አሳውቋል።
ፍርድ ቤቱ ፓርቲው በ28 ምርጫ ወረዳዎች ምርጫ እንዲደገም ያቀረበውን አቤቱታ ሲመረምር ቆይቶም ፓርቲው ያቀረበውን የይግባኝ አቤቱታ ተቀብሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ይዞ እንዲቀርብ ተወስኗል።
ምርጫ ቦርድ ለሐምሌ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ምላሹን ይዞ መቅረብ እንዳለበትም ፍርድ ቤቱ በዛሬው እለት መበየኑ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ ኢዜማ ከዚህ ቀደም ለምርጫ ቦርድ ያስገባቸውን የቅሬታ ማስገቢያ ቅፆች ቅጂም ከሐምሌ 30 በፊት ቦርዱ ለፍርድ ቤቱ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተላልፏል።
ኢዜማ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስገባው የይግባኝ አቤቱታ ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል ባላቸው 28 የምርጫ ወረዳዎች ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲያስተላልፍለት በመጠየቅ ነው፡፡
ኢዜማ በነዚህ ምርጫ ወረዳዎች የተፈጸሙ ግድፈቶች አሉ በሚል ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዱ የሚታወስ ነው።
ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ ያስገባው ኢዜማ፤ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰድኩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀርብኩለትን ቅሬታዎች እንዲሁም ማስረጃዎችን ሳይገመግም ውሳኔ ስላስተላለፈብኝ ነው ብሏል፡፡
ኢዜማ ሰኔ 14 በተደረገው አገራዊ ምርጫ ከድምጽ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ከቀበሌ እስከ ክልል ባሉ የገዢው ፓርቲ አመራሮች፣ ከቀበሌ ሚሊሻ እስከ ክልል ልዩ ኃይል ድረስ ባሉ የጸጥታ አስከባሪዎች፣ ምርጫ አስፈጻሚዎችና ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች አማካኝነት ምርጫው ሲስተጓጎል ነበር ሲል ከሷል፡፡
ይህም በምርጫው ውጤት ላይ ተጽእኖ አሳድሯል ብሏል፡፡
ለዚህም በቂ የሆነ የሰው፣ የሰነድ የቪዲዮና የምሥል ማስረጃዎችን ማጠናቁሩንም ገልፆ ነበር፡፡