አራት የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዋ ሲሞን ከቶኪዮ የፍፃሜ ውድድር ራሷን አገለለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካዊቷ የጂምናስቲክ አትሌትና አራት ጊዜ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚዋ ሲሞን ባይልስ በቶኪዮ በነገው ዕለት ከሚደረገው የጂምናስቲክ የፍፃሜ ውድድር ራሷን ማግለሏን አስታውቃለች።
በአለም በጂምናስቲክ ስፖርት ዘርፍ የምንጊዜውም ምርጥ የሚል ስም ማትረፍን የቻለችው አትሌቷ ከሴቶች ቡድን የፍፃሜ ውድድር ራሷን ያገለለችው በአዕምሮ ጤንነቷ ላይ ማተኮር ስላለባት መሆኑንም ተናግራለች።
የአሜሪካ ኦሊምፒክ ቡድን መሪ እና አትሌቶችም ሲሞን ለአእምሮ ጤንነቷ ቅድሚያ ለመስጠት መወሰናቸውን አድንቀዋል።
የ 24 ዓመቷ አትሌት በቶኪዮ አምስቱን የግለሰብ የጂምናስቲክ ዘርፍ ፍፃሜዎች ደርሳለች።
በመጪው ሃሙስ 'ኦል አራውንድ' በተባለው ውድድር የቀደመ አሸናፊነቷን ለማስጠበቅ መሳተፍ ነበረባት። ከዚያ በኋላም በመጪው እሁድ፣ ሰኞና ማክሰኞም ሌሎች በጂምናስቲኩ ዘርፍ ባሉ ውድድሮችም መሳተፍ አለባት።
የአሜሪካ ጂምናስቲክስ እንዳለው "ሲሞን በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄዱት የግለሰብ የፍፃሜ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ወይም ላለመሳተፍ መቻሏንም በተመለከተ በየቀኑ ትገመገማለች" ብሏል።
"እኛ የሲሞንን ውሳኔ በሙሉ ልብ እንደግፋለን እናም ለጤንነቷ ቅድሚያ በመስጠት ድፍረቷን እናደንቃለን ። ድፍረቷ አሁንም ለምን ለብዙዎች አርአያ እንደምትሆን አሳይ ነው" ብሏል።
ሲሞን ከቡድኑ የፍፃሜ ውድድር ራሷን ከማግለሏ በፊት በአንደኛው የጂምናስቲክ ውድድር አይነት ዝቅተኛውን ነጥብ አስመዝግባለች ተብሏል።
ምንም እንኳን ከውድድሩ መድረክ ብትወጣም የኦሎምፒክ ቡድኗን ለመደገፍ ተመልሳ መምጣቷ ተገልጿል።
የኦሎምፒክ ቡድኗ ሩሲያን ተከትሎ የብር ሜዳልያ ማግኘት ችሏል። ለሲሞን ይሄኛው ስድስተኛው የኦሎምፒክ ሜዳልያዋ ሲሆን 30 የአለም ሻምፒዮና ሜዳልያም ማግኘት የቻለች አትሌት ናት።
ከውድድሩም በኋላ " ከውድድሬ በኋላ መቀጠል አልፈለግኩም። በአዕምሮ ጤንነቴ ላይ ማተኮር አለብኝ። በአሁኑ ወቅት የአዕምሮ ጤንነት ሁኔታ በስፖርት ውስጥ በጣም የተስፋፋ ይመስለኛል። " ብላለች።
"ዓለም የሚፈልገውን ብቻ ማድረግ የለብንም። ሰውነታችንና የአዕምሮ ጤንነታችንን ልንጠብቅ ይገባል" በማለትም መልዕክቷን አስተላልፋለች።
"ከእንግዲህ በራሴ ላይ እምነት የለኝም። ምናልባት በዕድሜ እየተለቅኩ ስለሆነ ሊሆን ይችላል። ሁሉም ሰው ስለኔ ትዊት በሚያደርግባቸው የተወሰኑ ቀናት የዓለምን ሸክም ሁሉ የተሸከምኩ ይመስለኝ ነበር"
"እኛ አትሌቶች ብቻ አይደለንም። በቀኑ መጨረሻ እኛም እንደሌላው ብዙ ስሜት የሚሰማን ሰዎች ነን እናም አንዳንድ ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለንም ልናይ ይገባል" በማለትም መልዕክቷን አስተላልፋለች።












