ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሳ የደቡብ አፍሪካው ነውጥ እንዲነሳ 'አስቀድመው የወጠኑ' እንዳሉ ተናገሩ
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሳ በመላው አገሪቱ የተነሳው ነውጥ የታቀደና ዴሞክራሲ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው አሉ።
የቀድሞው ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ መታሰራቸውን ተከትሎ በተነሳው አለመረጋጋት ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 212 ደርሷል።
ለቀናት የመገበያያ ማዕከሎች ሲዘረፉ፣ ሲቃጠሉም ነበር። ይህም የምግብ እጥረት አስከትሏል። ፖሊሶች መደብሮችን በተጠንቀቅ ለመጠበቅም ተገደዋል።
የዙማ ትውልድ ከተማ በሆነው ክዋዙሉ-ናታል አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ንብረት ተዘርፏል። 800 ሱቆችም መዘረፋቸውን የከተማው ከንቲባ ተናግረዋል።
ራማፎሳ ከተማውን በጎበኙበት ወቅት "ይህ አለመረጋጋት እና ዝርፊያ እንዲከሰት አስቀድመው የወጠኑ እንዳሉ ግልጽ ነው። ያዘጋጁትና ያስተባበሩትም ሰዎች አሉ" ብለዋል።
ፕሬዚደንቱ ነውጡ የደቡብ አፍሪካን ዴሞክራሲ ለማሰናከል ያለመ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
የረብሻው ቀስቃሾች ማንነት እንደታወቀ ቢገልጹም "እንከታተላቸዋለን" ከማለት በዘለለ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም።
የነውጡ መነሻ በሆነው ክዋዙሉ-ናታል የሚኖሩ ዜጎች ምግብ ለማግኘት ከጠዋት ጀምሮ ለመሰለፍ ተገደዋል።
ብዙ ነዋሪዎች ቤተሰቦቻችንን ምን እንመግባለን? የሚል ጭንቀት ውስጥ እንደገቡ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ለልጆች ፎርሙላ፣ ዳይፐርና ሌሎችም መሠረታዊ ቁሳቁሶች ማግኘት የተቸገሩ በርካቶች ናቸው።
በተጨማሪም የከተማው አውራ ጎዳናዎች በተቃዋሚዎች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።
መንግሥት የምግብ አቅርቦት እንዳይስተጓጎል ለማድረግ እየሞከረ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ረብሻውን እንዲያረግብ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ተሰማርቷል። ፖሊስም ኦክስጅን፣ መድኃኒትና ሌሎችም መሠረታዊ አቅርቦቶች ሲጓጓዙ ጥበቃ እያደረገላቸው ነው።
ፕሬዘዳንት ራማፎሳ ለሕዝቡ በቴሌቭዥን ባደረጉት ንግግር፤ የምግብ እጥረት እንደሌለ ገልጸው፤ ዜጎች በስጋት ምግብ እንዳያከማቹ አሳስበዋል።
ከ2,500 በላይ ሰዎች በነውጡ እጃችሁ አለበት ተብለው እንደታሰሩም አክለዋል።
አያይዘውም "በአንድነት ከቆምን ማንኛውም አይነት ነውጥ አገራችንን አያሰናክላትም። ዴሞክራሲያችንን፣ ሕይወታችንን፣ ደኅንነታችንን እንዲሁም ሕገ መንግሥታችንን መከላከል አለብን" ብለዋል።
በሙስና ወንጀል ለፍርድ የቀረቡት ዙማ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ባለማክበር የ15 ወራት እስር ሲፈረድባቸው ደጋፊዎቻቸው ነውጡን ቀስቅሰዋል።
ከክዋዙሉ-ናታል የተነሳው ተቃውሞ ወደ ጆሀንስበርግ፣ ጋውተንግ እና ሌሎችም ከተሞች ተስፋፍቶ በርካታ የንግድ ተቋማት ወድመዋል።