ትራምፕ በትዊተር፣ ጉግል እና ፌስቡክ ላይ ክስ መሰረቱ

ታትሟል

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጉግል፣ የትዊተር እና የፌስቡክ የሳንሱር ሰለባ ነኝ ሲሉ ክስ መስርተዋል፡፡

የተመሰረተው ክስ የሦስቱን ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚዎችንም ዒላማ አድርጓል፡፡

በደጋፊዎቻቸው የሚመራውን የካፒቶል አመጽ ተከትሎ ትራምፕ በህዝብ ደህንነት ላይ ስጋት ፈጥረዋል በሚል ጥር ወር ላይ ከማህበራዊ ድር አምባዎቻቸው ታግደዋል፡፡

ረቡዕ ዕለት ትራምፕ ክሱን "ለመናገር ነጻነታችን በጣም ድንቅ ዕድገት" ብለውታል፡፡

በኒው ጀርሲ ቤድሚንስተር ከሚገኘው የጎልፍ ሪዞርታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ትራምፕ የተሳሳተ መረጃን በማቅረብ ተከሰዋል በተባሉ የማህበራዊ ድር አምባ ኩባንያዎች እና በዴሞክራቶች ላይ ተሳልቀዋል፡፡

"ብሎክ ማድረግ እንዲቆም፣ ዝም ማስባል እንዲቆም፣ በጥቁር መዝገብ ላይ የማስፈር፣ ማፍረስ እና መሰረዝ እንዲቆም እንጠይቃለን" ብለዋል፡፡

ክሱ ሳንሱር እንዲቆም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ፕሬዚዳንትን ማገድ ከቻሉ "ማንም ላይ ሊያደርጉት ይችላሉ" ብለዋል ትራምፕ፡፡

ክስ ከተመሰረተባቸው የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መካከል አንዳቸውም በፍሎሪዳ ፌዴራል ፍርድ ቤት ስለቀረበው ክስ ምላሽ አልሰጡም፡፡

በትራምፕ መግለጫው ላይ የቀድሞ የትራምፕ ባለሥልጣናትና ለትርፍ ያልተቋቋመው የአሜሪካን ፈርስት ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ባልደረቦች በጋራ ተገኝተዋል፡፡

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከትዊተር እንዲታገዱ ያደረጋቸውን ጽሑፍ "በጣም በፍቅር የተሞላው ዓረፍተ ነገር" ብለውታል፡፡

ትዊተር እንደገለጸው ትራምፕ "አመጽን በመደገፍ" በሚል ለእገዳው ምክንያት የሆኑበትን ትዊቶች በካፒቶል ሂል ከተከሰተው ሁከት ከሁለት ቀናት በኋላ የተላለፉት ናቸው።

በተደጋጋሚ ምርጫውን በጆ ባይደንን ደግፎ ተጭበርብሯል ብለው ያለማስረጃ ካቀረቡት ተደጋጋሚ መልዕክት በኋላ ነበር አመጹ የተከተለው።

በተመሳሳይ ረቡዕ ዕለት በኮንግረስ የሚገኙት የትራምፕ የሪፐብሊካን አጋሮች "ታላላቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ወደ ለመቆጣጠር" ስለማቀዳቸው የሚገልጽ ማስታወሻ ለቀዋል፡፡

አጀንዳው ኩባንያዎቹን "ለማፍረስ" እና "አንቀጽ 230" ተብሎ የሚጠራ ሕግ እንደገና እንዲሻሻል የሚጠይቅ ነው ፡፡

ትራምፕ ፕሬዝዳንት ሆነው ለመሰረዝ የሞከሩት ክፍል 230 በመሠረቱ እንደ ፌስቡክ እና ትዊተር ያሉ ኩባንያዎች ተጠቃሚዎች ለሚለጥፏቸው ነገሮች ተጠያቂ እንዳይሆኑ ያግዳቸዋል፡፡

ኩባንያዎቹን "አታሚ" ከመሆን ይልቅ "መድረክ" እንደሆኑ ይቆጥራቸዋል።

ትራምፕ ረቡዕ ዕለት ህጉን በመተቸት "ይህ በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ማንም ያላገኛቸው የተጠያቂነቶች ጥበቃ ነው" ብለዋል ፡፡

ክሱ በሕግ ባለሙያዎች ተችቷል። ትራምፕ ለመገናኛ ብዙኃን ትኩረት የሚሰጡ ክሶችን የማቅረብ ልማድ እንዳላቸው ጠቁመው በፍርድ ቤት ቀርበው በህግ ሊከላከሉ ይገባል ብለዋል።

በነጻነት መናገር ላይም ጥያቄ የሚያነሱት ተንታኞች የሚከሷቸው ኩባንያዎች ባላቸው ይዘት ላይ የመወሰን ህጋዊ ከለላ አላቸው ይላሉ፡፡