በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ3 በላይ የውጭ አገር ተጫዋቾች ማስፈረም ተከለከለ

ታትሟል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2014 ዓ.ም የውድድር ዘመን የትኛውም የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ከሦስት በላይ የውጭ አገር ተጫዋቾች ማስፈረም እንደማይችል አስታወቀ።

ከዚህ በፊት በነበረው የውጭ አገር ተጫዋቾች የዝውውር መመሪያ መሠረት አንድ ክለብ እስከ አምስት ድረስ የውጭ አገራት ተጫዋቾች ማስፈረም ይችል ነበር።

በመጪው ዓመት በሚጀመረው በአዲሱ የውድድር ዘመን ግን ቁጥሩን በመቀነስ ሦስት ተጫዋቾች ብቻ ማስፈረም እንዲችሉ መደረጉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ኃላፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የነበረውን የአገሪቱን የተጫዋቾች ዝውውር መመሪያን ለማሻሻል በማሰብ ረቂቅ ሀሳብ ለክለቦች አቅርቦ እንደነበር አቶ ባሕሩ አስታውሰዋል።

በዚህም መሠረት ማንኛውም ክለብ አገር በቀል ተጫዋቾችን ከማበረታታት አንጻር የውጭ ተጫዋቾች ቁጥር አምስት መሆኑ የሚኖረውን ጫና ፌዴሬሽኑ እንደተገነዘበ አመልክተዋል።

"አንዳንድ ክለቦችም አገር በቀል ተጫዋቾች ላይ በደንብ ሲሰሩ አይታይም። ይሄ አካሄድ ደግሞ የሆነ ቦታ ላይ ሊቆም ይገባል'' ሲሉ አቶ ባህሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

''አገር በቀል ተጫዋቾችን ለማፍራትና ለማበረታታት ሲባል ደግሞ መሰል እርምጃዎችን መውሰድ በጣም አስፈላጊ ነው'' ብለዋል።

አክለውም ባለፈው ዓመት በተጀመረው ሥራ ከሦስት በላይ የውጭ አገር ተጫዋቾች ያሏቸው ክለቦች የአንድ ዓመት ኮንትራት ብቻ እንዲያስፈርሙ መደረጉንም ገልጸዋል።

''በአሁኑ ጊዜ ከሦስት በላይ ተጫዋቾች የያዘ ክለብ የለም፤ ወይም የሁሉም የውጭ አገር ተጫዋቾች ኮንትራታቸው ክረምት ላይ ያልቃል። ስለዚህ ክለቦች በአዲሱ የ2014 የውድድር ዓመት የሚፈልጓቸውን ሦስት ተጫዋቾች ኮንትራት ማራዘምም ሆነ አዲስ ማስፈረም ይችላሉ።"

"ውሳኔው አሁን ላይ ይፋ ሆኖ ክለቦች እንዲያውቁት ተደረገ እንጂ ከአምና ጀምሮ ክለቦች ከሚይዟቸው ተጫዋቾች መካከል ከአንድ በላይ ኮንትራት አላፈራረምንም። በ2014 ተግባራዊ የሚደረግ አዲስ ውሳኔ ስላለ ቀድመን ስንዘጋጅበት ነበር'' ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ውሳኔው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ክለቦች እንዲያውቁትና የራሳቸውን ግብአት እንዲጨምሩበት ተደርጓል ብለዋል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ኃላፊው።

"የተሻሻለውን የተጫዋቾች ዝውውር መመሪያ ለሁሉም ክለቦች ሰጥተን ሀሳባቸውን ተቀብለናል። እነሱ በሰጡን አስተያየት ላይ ተመስርተንም ነው ይህንን ውሳኔ ያስተላለፍነው። እንደውም ለክለቦቹ በላክነው በዚህ አዲስ መመሪያ መሰረት የውጭ አገር ግብ ጠባቂዎች እንዳይገቡ ጭምር ይከለክል ነበር'' ብለዋል።

ይሁን እንጂ እንደ አቶ ባሕሩ ገለጻ፤ ግብ ጠባቂዎችን ጉዳይ በተመለከት መመሪያው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ክለቦች ምን ያህል ግብ ጠባቂ ላይ ሰርተዋል? ገበያው ላይ ምን አይነት ግብ ጠባቂዎች አሉ? የሚሉት ጉዳዮች ከግምት ገብተው ለጊዜው ግብ ጠባቂዎችን በተመለከተ የተላለፈው ውሳኔ እንዲገታ ተደርጓል።

"ከግብ ጠባቂዎች ጋር በተያያዘ እንደ አገር ከፍተኛ የስልጠና ሥራ ማከናወን ይኖርብናል። በቀጣይም ከክለቦች ጋር በመሆን ብዙ ሥራዎችን እንሰራለን። የአሰልጣኞች ስልጠና፣ የግብ ጠባቂዎች ስልጠና እንዲሁም የሌሎች አገራት ተሞክሮን ከግምት አስገብተን የበረኞችን ጉዳይ መፍትሄ እንሰጠዋለን።''

እነዚህ ጉዳዮች በሙሉ መልስ ማግኘት የሚችሉ ከሆነ ከግብ ጠባቂዎች ጋር በተያያዘ የተዘጋጀው መመሪያም ተግባራዊ የሚሆንበት ሁኔታ እንደሚፈጠር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ኃላፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን ተናግረዋል።

ፌዴሬሽኑ በአገሪቱ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ አንድ ቡድን ሊኖሩት የሚገቡትን የውጭ አገር ተጫዋቾች ቁጥርን ከመገደቡ በተጨማሪ በከፍተኛ እና በ1ኛ ሊግ ተሳታፊ የሚሆኑ ክለቦች ደግሞ ምንም ዓይነት የውጭ አገር ተጫዋቾች ማስፈረም እንደማይችሉ ክልከላ ጥሏል።