ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሸራ ቤት ውስጥ ተጠልለው የሚኖሩ ቤተሰቦቹ ላይ የእሳት ቃጠሎ ያደረሰው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ
በሸራ ቤት ውስጥ ተጠልለው የሚኖሩ ቤተሰቦቹ ላይ የእሳት ቃጠሎ ያደረሰው ግለሰብ በስምንት ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን ከጠቅላይ አቃቤ ህግ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ባወጣው መግለጫ ግለሰቦቹ በሸራ ቤት ውስጥ ተጠልለው የሚኖሩና ሻይና ቡና በማፍላት የሚተዳደሩ ናቸው።
ግርማ ታደሰ የተባለው ይህ ተከሳሽ ከምሽቱ 1፡40 አካባቢ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው አሜሪካን ግቢ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለቤቱና ልጆቹ ባሉበት የሸራ ቤት ውስጥ እንዳሉ በሃይላንድ ፕላስቲክ ውስጥ ነዳጅ በመያዝ የሸራ ቤቱ የውጨኛውን ክፍል እና በቤቱ ውስጥ በምድጃ ተያይዞ በነበረው ከሰል ላይ ነዳጁን አርከፍክፏል።
የሸራ ቤቱ በእሳት የተያያዘ ሲሆን በወቅቱ በቤቱ ውስጥ የነበሩት ሁለቱ ልጆቹ ባለቤቱና በአንድ ተስተናጋጅ ግለሰብ ላይ የሁለተኛና መጠነኛ የሆነ የመጀመርያ የእሳት ቃጠሎ በተለያየ የሰውነት ክፍሎቻቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ ላይ የሰዎችን ምስክርነት ቃል እና የተበዳዮችን የጉዳት መጠን የሚገልፅ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የቀረበን የሰነድ ማስረጃም መቅረቡ ተገልጿል።
የእሳት ቃጠሎ በማድረስ የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አዲስ ከተማ ምድብ ወንጀል ችሎትም ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቶታል።
ግለሰቡም ጥፋተኛነቱን አምኖ ቃሉን የሰጠ ሲሆን "ድርጊቱን የፈፀምኩት በወቅቱ አልኮል ጠጥቼ ስለነበረ ነው በድርጊቴ ተፀፅቻለሁ ጥፋተኛ ነኝ" ማለቱን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስፍሯል።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ቢሰጥም ተከሳሽ መከላከል ባለመቻሉ ሰኔ 29/2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽን ጥፋተኛ ነህ ሲል በ8 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑም ሰፍሯል።