ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምርጫ 2013፡ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በምርጫ ክልላቸው በከፍተኛ ድምፅ አሸነፉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለፓርላማ በተወዳደሩበት የኦሮሚያ ክልል የጎማ 2 ምርጫ ክልል ማሸነፋቸውን የኢትኦጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትናንትናው ዕለት አስታውቋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሊቀ መንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በከፍተኛ ድምጽ 76 ሺህ 892 ድምጽ በማግኘት የተወካዮች ምክር ቤት አባልነታቸውን አረጋግጠዋል።
ይህንንም ድምጽ ያገኙት በ85 የምርጫ ጣቢያዎች ከተመዘገቡት 79 ሺህ 295 ተመዝጋቢዎች መካከል ነው።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተወዳደሩት ዳጊም ዋሪሶ ከእናት ፓርቲ እንዲሁም ካሊድ ጀማል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ኢዜማ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ የምርጫ ክልሎችን ውጤት ይፋ በማድረግ ላይ ይገኛል።
በዚህም መሰረት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የቀድሞ ፕሬዚዳንት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በተወዳደሩበት በአማራ ክልል በባሕር ዳር ከተማ ምርጫ ክልል ማሸነፋቸውን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
የአብን ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ ገዢው ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ ስምንት የፓርቲ ተወካዮች በተወዳደሩበት 47 ሺህ 483 ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
በባሕር ዳር የተመዝጋቢ መራጮች ቁጥር ከ137 ሺህ በላይ ነው።
በባሕር ዳር ከተማ ምርጫ ክልል የተወዳደሩት ፓርቲዎች አብን፣ እናት፣ ሕብር፣ ኢዜማ፣ ኢዴኃን፣ የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ፣ ብልጽግና፣ መኢአድ፣ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲዎች ናቸው።
ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደው ምርጫ ላይ የተገኘውን ውጤት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማጣሪያ በማድረግ ይፋ እያደረገ ይገኛል።
ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ተካሂዶ የነበረ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ደግሞ በመጪው ጳጉሜ 01/2013 ዓ.ም ይካሄዳል።
ባለፈው ዓመት ሊካሄድ ታስቦ ከ37 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተመዘገቡበት ምርጫ ዘንድሮ ሰኔ 14፣ 2013 ዓ.ም ተደርጓል።