ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስቃይ ሲፈጽምባት የነበረ ባሏን የገደለችው ፈረንሳያዊት ከእስር ተለቀቀች
በባለቤቷ ለረጅም ጊዜ የተፈጸመበት ስቃይ ፈረንሳይ ውስጥ ከባድ ድንጋጤን ፈጥሮ የነበረችው ቫሌሪ ባኮ ባሏን በመግደል ወንጀል ጥፋተኛ ብትባልም ከእስር እንድትለቀቅ ፍርድ ቤት ወሰነ።
በሦስት ዓመት ገደብ የአራት ዓመት እስራት የተፈረደባት ቫሌሪ በእስር የቆየችበት ያለፈው አንድ ዓመት ከቅጣቷ ውስጥ ተቆጥሮላት ተለቃለች።
ባኮ ዐቃቤ ሕግ ጥፋተኛ እንድትባል በጠየቀበት ወቅት ፍርድ ቤት ውስጥ ራሷን ስታ ወደቃ ነበር። ሆኖም ምህረት ተሰጥቷት ከእስር እንድትፈታ ተደርጓል።
ቫሌሪ ባኮ ከአራት ዓመት በፊት ነበር በገዛ ሽጉጡ ተኩሳ የገደለችው ይህንንም ድርጊቷን አምናለች።
የ40 ዓመቷ ቫሌሪ ከ12 ዓመቷ ጀምሮ መጀመሪያ የእንጀራ አባቷ በኋላ ደግሞ ባሏ በነበረው ዳንኤል ፖሌቴ እንዴት እንደተሰቃየች ገልጻለች።
ፖሌቴ ለዓመታት ከሌሎች ወንዶች ጋር በወሲብ ንግድ ላይ እንድትሠማራ ያስገደዳት ነበር። በመጨረሻም ሴት ልጃቸውን ስለመጉዳት ማውራት በጀመረ ጊዜ ድርጊቱን መፈጸሟን አስታውቃለች።
ከ700 ሺህ በላይ ሰዎች ከእስር እንድትፈታ የሚጠይቅ ፊርማ አሰባስበዋል።
'ፍትህ ሰፍኗል'
ከፍርድ ቤት ስትወጣ መልካም ምኞታቸውን የሚያስተላልፉ ሰዎች "ብራቮ!" እያሉ በጭብጨባ ተቀብለዋታል። እሷም ለጋዜጠኞች ጉዳዩ አለመጠናቀቁን ተናግራለች።
"እፎይታ አላገኘሁም ... በአካልም ሆነ በመንፈስ ሙሉ በሙሉ ተሰናክያለሁ" ስትል ወደ አራት ልጆቿ መመለስ እንደምትፈልግ ተናግራለች።
ቫሌሪ ፍርድ ቤት ስትመላለስ አንድ ዓመት ያህል ያሳለፈች ሲሆን ከዳኞች ውሳኔ በፊት ጠበቆቿ መፈታት ብቻ ሳይሆን ከቀረበባት ክስ ነጻ መሆን አለባትም ብለዋል።
ጠበቃዋ ናታሊ ቶማሲኒ "ይህቺ ሴት ዛሬ ማታ ወደ ልጆቿ መመለሷ ለእኔ ትልቅ ድል ነው። እናም በጣም ተደስቻለሁ" ብለዋል። ጠበቃዋ እንደ ካናዳ ሁሉ ራስን መከላከል በፈረንሳይም ሕጋዊ ተቀባይነት እንዲያገኝ ትፈልጋለች።
ቀደም ሲል ዐቃቤ ሕግ ኤሪክ ጃሌ በምሥራቃዊቷ የቻሎን-ሱር ሳን ፍርድ ቤት ቫሌሪ ነጻ ብትባልም ጥፋተኛ መባሏ አስፈላጊ ነው ሲል ተከራክሯል።
"ፍርድ ቤት ለሥልጣኔ ዕሴቶች ይቆማል። ከእነዚህም መካከል የሕይወት ጥበቃ አንዱ ነው። ሰዎች ፍትሕን በእጃቸው ካስገቡ ሁሉም ሰው ከሌላው ጋር ጦርነት ውስጥ ነው ማለት ነው" ብለዋል።
መታሰሯ ግን ማንንም ሰው ከጥቃት ነጻ እንደማያደርግና ብትወጣም ድጋሚ ወንጀል የመፈፀም ዕድሏ አነስተኛ ነው ሲሉም አክለዋል። ቫሌሪ አሁን የተፈረደባትን የአራት ዓመት ሳይሆን የአምስት ዓመት ቅጣት እንድትከናነብ ጠይቀው ነበር።
በፈረንሣይ ድንጋጤን የፈጠረ ጉዳይ
የቫሌሪ ባኮት ጠበቆች ቀደም ሲል "ለ25 ዓመታት በደረሰባት ከፍተኛ ጥቃት እና ልጇም ቀጣይ ተጠቂ ትሆናለች በሚል ስጋት" ባሏን ለመግደል እንደተነሳሳች ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
የእሷ ጉዳይ ከሌላዋ ፈረንሳዊት ጃኩሊን ሱቬጅ ጋር ተመሳስሏል። ሱቬጅ ከ47 ዓመታት እንግልት በኋላ ባለቤቷን በጥይት በመግደሏ እንድትታሰር ተፈርዶባታል።
እአአ በ2016 ሱቬጅ ከ10 ዓመት እስሯ ሁለት ዓመቱን በማረሚያ ቤት ካሳለፈች በኋላ ፕሬዝዳንታዊ ምህረት አግኝታለች። ተመሳሳይ የሕግ ቡድን ነው የቫሌሪ ባኮን የፍርድ ቤት ጉዳይ መከታተል የቀጠለው።
ከቫሌሪ በ25 ዓመት የሚበልጣት ባሏ ፓሌቴ በ1990ዎቹ በእሷ ላይ ጥቃት በመሰንዘሩ ለሁለት ዓመት ተኩል ታስሮ ነበር። በኋላ ወደ ቤተሰቡ ቤት ተመልሳ በ17 ዓመቷ አስረገዛት።
በቅርቡ ስለህይወት ታሪኳ በጻፈችው መጽሐፍ ላይ "ሁል ጊዜም እንደምትፈራ" እና ይህም "ማብቃት ነበረበት" ብላ እንደምታስብ ጽፋለች። ባለቤቷ በተደጋጋሚ በሽጉጥ ለመግደል እንዳስፈራራት ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች።
ለ14 ዓመታት በሴተኛ አዳሪነት እንድትሠራ እንዳስገደዳትም ተናግራለች። በቤተሰቧ ፔጆ መኪና ውስጥ ጭምር ከደንበኞቿ ጋር ወሲብ እንድትፈጽም እንዴት እንደተገደደች በዝርዝር ለፍርድ ቤት ቀርቧል።