በፓኪስታን ለፖሊስ በርገር በነጻ አልሰጡም የተባሉ ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ታትሟል

በፓኪስታን በሚገኘው ፈጣን ምግብ ቤት የሚሠሩ 19 ቱም ሠራተኞች ለፖሊሶች በርገር በነጻ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

በላሆር የሚገኘው እና ብዙ ቅርንጫፍ ያሉት ጆኒ እና ጁግኑ ሠራተኞች ቅዳሜ በቁጥጥር ሥር ውለው ሌሊቱን አሳልፈዋል፡፡

"ይህ የመሰለ ነገር ምግብ ቤታችን ሲከሰት የመጀመሪያው አይደለም" ብሏል ድርጅቱ በሰጠው መግለጫ፡፡

ዘጠኝ የፖሊስ መኮንኖች በጉዳዩ በመሳተፋቸው ከሥራ ታግደዋል፡፡

የአካባቢው ፖሊስ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ኢናም ጋኒ የፖሊሶቹን መታገድ በትዊተር አስታውቀው "ማንም ሰው ህጉን ትቶ የራሱን ውሳኔ እንዲያስተላልፈፍ አይፈቀድለትም። ግፍን አንታገስም። ሁሉም ይቀጣሉ" ብለዋል፡፡

ጆኒ እና ጁግኑ በፌስቡክ ገጹ እንዳስታወቀው ችግሩ ከመከሰቱ ከሁለት ቀናት በፊት የፖሊስ መኮንኖች ወደ ምግብ ቤቱ በመሄድ በርገር በነጻ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

"የተለመደውን የፖሊስ መኮንኖቹን የነጻ በርገር ጥያቄ ውድቅ በመሆኑ ሥራ አስኪያጆቻችንን በማስፈራራት ሄደዋል። በሚቀጥለው ቀን ተመልሰው ሠራተኞቻችንን መሠረተ ቢስ በሆነ ክርክር የበለጠ አዋክበዋል እና ጫና አድርገዋል" ብሏል በመግለጫው፡፡

እአአ ሰኔ 11 "የፖሊስ መኮንኖች ወደ ቅርንጫፋችን መጥተው ምንም ምክንያት ሳይገልጹ ሥራ አስኪያጅያችንን ወደ እስር ቤት ወስደዋል፡፡ ከዚያም የተቀሩትን ሥራ አስኪያጆች ጨምሮ ሁሉንም የወጥ ቤታችን ሠራተኞች በመያዝ መላውን ቅርንጫፋችንን ባዶ አደረጉት።".

ምግብ ቤቱ በተጨማሪም ሠራተኞቹን ማዕድ ቤቱን ለመዝጋት አልተፈቀደላቸውም ብሏል።

"መጥበሻዎች እየተጠበሰባቸው፣ ደንበኞችም ትዕዛዛቸውን እየጠበቁ ነበር" ብሏል፡፡ሠራተኞቹ ለሰባት ሰዓታት ያህል በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን የፖሊስ መኮንኖቹ "ነጻ በርገር አልሰጣችሁንም በሚል እያስጨነቋቸው እና እየገፏቸው ነበር" ብሏል ፡፡

ቀደም ሲል የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካህን የአከባቢው ፖለቲከኞች የፖሊስ ጣቢያዎችን እንዲያስተዳድሩ "ሽፍቶችን" መሾማቸውን በመግለጽ የፑንጃብ ክልል የፖሊስ ኃይል እንዲሻሻል ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡