ሜዳ ላይ ተዝለፍልፎ የወደቀው ክርስቲያን ኤሪክሰን መንቃቱ ተገለጸ

ታትሟል

ከፊንላንድ ጋር በተደረገው የዩሮ 2020 ውድድር ሜዳ ላይ ተዝለፍልፎ የወደቀው የዴንማርኩ አማካይ ክርስቲያን ኤሪክሰን ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ነቅቷል ብሏል የዴንማርክ እግር ኳስ ማህበር፡፡

የ 29 አመቱ የኢንተር ሚላን ተጫዋች የጤንነቱ ሁኔታ "የተረጋጋ" መሆኑን የውድድሩ አዘጋጅ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር (ዩኤፋ) ገልጿል፡፡

የቀድሞው የስፐርስ ተጫዋች ሜዳ ላይ ወድቆ ድንገተኛ ህክምና ከተደረገ በኋላ በኮፐንሃገን የነበረው ጨዋታ ለእረፍት የተወሰኑ ደቂቃዎች ሲቀሩት ተቋርጧል፡፡

ጨዋታው ከሰዓታት በኋላ ተጀምሮ ፊንላንድ የምድብ ሁለቱን ጨዋታ 1-0 አሸንፋለች፡፡

ጨዋታውን ለመቀጠል ወደ ሜዳ የተመለሱት የዴንማርክ ተጨዋቾች ከተጋጣሚያቸው ድጋፍ አግኝተዋል፡፡

ዩኤፋ "የሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾች ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ ጨዋታውን እንደገና ለመጀመር መስማማቱን" ገልጿል፡፡

የመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ አምስት ደቂቃ ጨዋታው ተከናውኖ ተጫዋቾቹ የአምስት ደቂቃ እረፍት አድርገው ሁለተኛውን አጋማሽ ተጫውተዋል፡፡

የዴንማርክ እግር ኳስ ማህበር ባልደረባ የሆኑት ፒተር ሞለር ለዴንማርክስ ሬዲዮ "እሱን [ኤሪክሰንን] አግኝተናል። ተጫዋቾቹ ክርስቲያንን አነጋግረዋል፡፡ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው። ተጫዋቾቹም ጨዋታውን ለክርስቲያን ይጫወታሉ" ብለዋል፡፡

የዴንማርክ ዋና አሰልጣኝ ካስፐር ሁልማድ ከጨዋታው መልስ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እያነቡ ነበር፡፡

"በእውነቱ በሕይወታችን ውስጥ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ምን እንደሆኑ ሁላችንም የተረዳንበት በጣም ከባድ ምሽት ነበር። ትርጉም ያላቸው ግንኙነቶች ናቸው፡፡ እነዚያም ለእኛ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ እነሱም ቤተሰብ እና ጓደኞች ናቸው" ብለዋል፡፡

"ሁሉም ነገር፣ ሁሉም ነገር፣ ሁሉም ነገር - የሁሉም ሃሳብ ከክርስቲያን እና ከቤተሰቡ ጋር ናቸው፡፡" ብለዋል።

የዩኤፋ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሴፈሪን "እንደዚህ ያሉ ሁኔታዎች በህይወት ውስጥ ያሉትን ነገሮች ወደ ተለያዩ ዕይታ ያስገባሉ፡፡ ለክርስቲያን ሙሉ እና ፈጣን ማገገምን እመኛለሁ። ለቤተሰቦቹ ጥንካሬ እና እምነት እንዲኖራቸው እጸልያለሁ" ብለዋል፡፡

"በእነዚህ ጊዜያት የእግር ኳስ ቤተሰቡ አንድነት በጣም የተጠናከረ ሲሆን እርሱ እና ቤተሰቦቹ የሁሉንም ሰው መልካም ምኞት እና ጸሎት ይዘው ይኖራሉ፡፡ የሁለቱም ቡድኖች ደጋፊዎች ስሙን ሲጠሩ ሰምቻለሁ፡፡ እግር ኳስ የሚያምር ሲሆን ክርስቲያን ደግሞ በሚያምር ሁኔታ ይጫወተዋል፡፡"

የቅዳሜ ሌላኛው የምድብ ሁለት ጨዋታ በቤልጂየም እና በሩሲያ መካከል በተያዘው ሰዓት የተካሄደ ሲሆን ቤልጂየም 3-0 አሸንፋለች፡፡

ቤልጂየማዊው አጥቂ ሮሜሉ ሉካኩ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን የመጀመሪያውን ጎል ሲያስቆጥር ለቴሌቪዥን ካሜራዎች "ክሪስ እወድሃለሁ" በማለት ለኢንተር የቡድን አጋሩ ስሜቱን አጋርቷል፡፡

ሉካኩ ከጨዋታው በኋላ "በጨዋታው ደስ ቢለኝም መጫወት ከብዶኛል ምክንያቱም አእምሮዬ ከቡድን አጋሬ ክርስቲያን ኤሪክሰን ጋር ነበር፡፡

ስለፈራሁ በጣም ነበር ያለቀስኩት፡፡ ከባድ ጊዜዎችን አብረን እንኖራለን። ከቤተሰቦቼ ጋር አብሬ ካሳለፍኩት በላይ ከእሱ ጋር ብዙ ጊዜ አሳልፌያለሁ፡፡ ጸሎቴ ከእሱ፣ ከሴት ጓደኛው፣ ከሁለቱ ልጆቹ እና ከቤተሰቦቹ ጋር ነው" ብሏል፡፡

የዴንማርክ እና የፊንላንድ ጨዋታ ችግሩ ሲከሰት ወደ እረፍት የተቃረበ እና ግብ አልተቆጠረበትም ነበር፡፡

የማንቸስተር ተወላጁ ዳኛ አንቶኒ ቴይለር በፍጥነት የህክምና ድጋፍ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ተጨዋቾቹ ከሜዳው ከመውጣታቸው እና ጨዋታው ለሌላ ጊዜ ከማስተላለፉ በፊት ኤሪክሰን ሜዳ ላይ ህክምና ተሰጥቶታል፡፡

"የዴንማርክ ክርስቲያናዊ ኤሪክሰን በደረሰበት ድንገተኛ የህክምና አደጋ ጨዋታው ተቋርጧል፡፡ ተጫዋቹ አሁን በሆስፒታል ሲሆን በተረጋጋ ሁኔታ ላይ ነው" ብሏል የዩኤፋ መግለጫ፡፡

"ዩኤፋ ለክርስቲያን ኤሪክሰን የተሟላ እና ፈጣን የማገገም ምኞቱን እየገለጸ ሁለቱም ቡድኖች አርአያ ለሆኑበት ሥራ ምስጋና ለማቅረብ ይፈልጋል፡፡"

የመጀመሪያው አጋማሽ መጨረሻ አካባቢ የመልስ ኳስ ወደ ኤሪክሰን ሲወረወር ነበር ችግሩ የተከሰተው።

የተጨነቁ የቡድን አጋሮቹ ከበውት ሲታዩ በፓርከን ስታዲየም የተደናገጡት ደጋፊዎች ተጫዋቹ ሲታከም ሲመለከቱ ነበር፡፡

የኤርኪሰን ክለብ ኢንተር በትዊተር ገጹ ላይ "ፎርዛ ክሪስ ሁሌም ሃሳባችን ከአንተ ጋር ናቸው" ብሏል፡፡

የቀድሞ ቡድኑ ቶተንሃም "ክሪስቲያን ቶሎ ወደ ጤንነትህ ተመለስ። መላው የስፐርስ ቤተሰብ ከአንተ ጋር ነው" ብሏል፡፡

ኤሪክሰን ኢንተር ሚላንን ጥር 2020 ከስፐርስ በ 16.9 ሚሊዮን ፓውንድ ተቀላቅሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ቡድኑ ከ 11 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን የጣሊያን ዋንጫ እንዲያነሳ አግዟል፡፡

የአያክስ ወጣት ቡድን ፍሬ የሆነው ተጫዋች በቶተንሃም ሰባት ዓመታትን ያሳለፈ ሲሆን በ 305 ጨዋታዎች 69 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡

ቢቢሲ የኤሪክሰን ህክምና ሲያገኝ የሚያሳዩ ምስሎች መታየታቸውን ተከትሎ ይቅርታ ጠይቋል፡፡

ቃል አቀባዩ "በቢቢሲ ያሉ ሁሉም ሰዎች ክርስቲያን ኤሪክሰን ሙሉ ለሙሉ እንደሚያገግም ተስፋ ያደርጋሉ፡፡"

"በተላለፉት ምስሎች ተበሳጭቶ የነበረን ማንኛውም ሰው ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡"

"የስታዲየም ስርጭቱን የሚቆጣጠረው አስተናጋጁ ዩኤፋ ሲሆን ጨዋታው እንደተቋረጠም በተቻለ ፍጥነት ስርጭቱን ከአየር ላይ አቋርጠናል" ብለዋል፡፡