ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፍሬዲ ፊገርስ፡ በሕጻንነቱ 'ተጥሎ' በቴክኖሎጂ ፈጠራ ሚሊየነር የሆነው ግለሰብ
ፍሬዲ ፊገርስ በ9 ዓመቱ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ከኮምፒውተር ጋር የተዋወቀው።
ኮምፒውተሩ ያረጀ እና የማይሠራ ነበር። ወደ ሥራ ፈጣሪነት እና ወደ ቴሌኮም ሚሊየነርነት ከቀየረው ቴክኖሎጂ ጋር በፍቅር የወደቀበት ጅምር ነበር።
የሕይወቱን አጀማመር ከባድነት ያየ አሁን የደረሰበት ይደርሳል ብሎ አይጠብቅም።
"ሁኔታዎች ማንነትዎን እንዲወስኑ አይፍቀዱ"፤ የ31 ዓመቱ ሥራ ፈጣሪ ፍሬዲ ለሌሎች ያለህ ምክር ሲባል የሚናገረው ብቸኛ ምክር ነው።
የተጣለው ልጅ
ስምንት ዓመት ሲሞላው ስለተወለደበት ሁኔታ አባቱ ናታንን ጠየቀ። ምላሹን መቼም አይረሳውም፡፡
"ስማ ፍሬዲ ፊት ለፊት ልመልስህ። ወላጅ እናትህ ስትጥልህ እኔ እና ቤቲ ማዬ ወደ ማሳደጊያ ማዕከል ልንልክህ አልፈለግንም። እናም በጉዲፈቻ አሳድገንሃል። አንተ ልጄ ነህ፡፡"
ፍሬዲ እንደተወለደ በፍሎሪዳ ገጠራማ አካባቢ በሚገኝ ቆሻሻ መጣያ አጠገብ ተጥሎ ተገኘ፡፡
"ያንን ሲነግረኝ 'ቆሻሻ ነኝ' ብዬ ያልተፈለግኩ ሆኜ ተሰማኝ። ትከሻዬን ይዞ 'ስማ መቼም ይህ እንዲረብሽህ አትፍቀድ' አለኝ፡፡"
ናታን ፊገርስ የጥገና ሠራተኛ እና የእጅ ባለሙያ ነው። ቤቲ ማዬ የእርሻ ሠራተኛ ናት። የሚኖሩት ደግሞ በሰሜን ፍሎሪዳ ወደ 8,000 ያህል ሰዎች በሚኖሩበት ኩዊንስ ነበር።
እአአ በ1989 ፍሬዲ ሲወለድ ዕድሜያቸው በ50 ዎቹ ውስጥ ነበር፡፡
ብዙ ልጆችን አፍርተዋል። ፍሬዲን በሁለት ቀን ዕድሜው ነበር በጉዲፈቻ የወሰዱት፡፡ ፍሬዲ እንደሚለው የሚያስፈልገውን ፍቅር ሁሉ ሰጥተውታል። በኩዊንስ ያሉ ሌሎች ልጆች ግን ጨካኝ ነበሩ፡፡
"ልጆቹ ያሾፉብኝ ነበር። 'የቆሻሻ መጣያው ልጅ'፣ 'ማንም አይፈልግህም' እና 'ቆሻሻ ነህ' ይሉኝ ነበር፡፡"
"አንዳንድ ጊዜ ከትምህርት ቤቱ አውቶቡስ ስወጣ ከኋላ ይዘው ወደ ቆሻሻ መጣያ እየጣሉ ይስቁብኝ ነበር፡፡"
አባቱ አውቶቡስ ማቆሚያው ድረስ እየመጣ ወደ ቤቱ የሚወስድበት ደረጃ ደርሷል። ልጆቹ ግን በናታን ላይም ያሾፉበት ነበር። ፍሬዲ "ሃ ሃ ባለከዘራውን አዛውንት ተመልከቱ" ይሉት ነበር በማለት ያስታውሳል፡፡
ለፍሬዲ ናታን እና ቤቲ ማይ ጀግኖች እና ታላቅ አርአያዎች ነበሩ፡፡
"አባቴ ሁሌም ሰዎችን ሲረዳ አያለሁ። በመንገድ ዳር ቆሞ የማያውቃቸውን ሰዎች ሲረዳ፣ ቤት ለሌላቸው ሲመግብ አያለሁ፡፡ የማይታመን ሰው ነበር። እኔን ተቀብለው ስላሳደጉኝ የእኔም ፍላጎት እንደእነሱ መሆን ነበር፡፡"
ኮምፒውተር ጠጋኙ ፍሬዲ
ቅዳሜና እሁድ ፍሬዲ እና ናታን "ቆሻሻ መጣያውን" ያስሳሉ። የተጣሉ ጠቃሚ ነገሮችን ይፈልጉ ነበር፡፡ ፍሬዲ ዓይኑ ኮምፒዩተር ላይ ነበር የሚያርፈው።
" 'የአንድ ሰው ቆሻሻ የሌላ ሰው ሀብት ነው' የሚል የቆየ አባባል አለ" ይላል ፍሬዲ። "ሁሌም በኮምፒውዩተሮች እማረክ ነበር፡፡ ሁሌም ጌትዌይ ኮምፒተርን እፈልግ ነበር። በዚያን ጊዜ ግን አቅም አልነበረንም" ሲልም ያስታውሳል።
ፍሬዲ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሆኖ ጉድዊል ወደሚባል ሰልባጅ ዕቃ ወደሚሸጥ ሱቅ ሄደው የተበላሸ ማኪንቶሽ ኮምፒውዩተር አገኙ፡፡
"ሻጩን አሳመንነው። 'እኔ በ24 ዶላር እሰጣችኋለሁ' ብሎ ኮምፒውተሩን ወደ ቤታችን ስለወሰድነው በጣም ተደሰትኩ፡፡"
ቀድሞውኑ ናታን ያጠራቀመውን ሬዲዮ፣ ሰዓቶች ወይም የቪዲዮ ማጫወቻዎችን መሰብሰብ ይወዳል። የተሰበረ ማክ ደግሞ ትኩረቱን ሳበው፡፡
ፍሬዲ "ቤት ገብቼ ስሞክረው አልሠራ አለኝ። ኮምፒውተሩን ከፋፈትኩት" ይላል፡፡
"ውስጡን ስመለከት የተሰበረ ካፓሲተር ተመለከትኩኝ። ከአባቴ ሬድዮ የተወሰነ ክፍል ወስጄ በመበየጃ ሰርኪዩት ቦርዱ ላይ ገጠምኩት፡፡"
ከ50 ገደማ ሙከራዎች በኋላ ኮምፒውተሩ ሠራ። በዚህ ጊዜ ፍሬዲ በሕይወቱ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ ሥራ መሥራት እንደሚፈልግ አወቅኩ ብሏል፡፡
"ያ ኮምፒውተር የሚያሾፉብኝ ሰዎች የሚያደርሱብኝን ሥቃይ በሙሉ አስወግዶልኛል" ይላል፡፡
ከትምህርት ቤት ሲወጣ ሁሌም ወደ አዕመሮው የሚመጣው "በፍጥነት ወደ ቤት ተመልሼ በኮምፒውተሬ መጫወት እፈልጋለሁ" የሚል ነው።
ችሎታው በሌሎች ዘንድ የታወቀለት በ12 ዓመቱ ነበር፡፡ ከትምህርት ሰዓት ውጭ ሌሎች ልጆች በመጫወቻ ስፍራው ሲጫወቱ ፍሬዲ በትምህርት ቤቱ የኮምፒውተር ቤተ ሙከራ ውስጥ የተበላሹ ኮምፒውተሮችን በመጠገን ጊዜውን ያሳልፋል፡፡
"ሃርድ ድራይቩ ከተበላሸ እቀይረው ነበር። ብዙ ሜሞሪ ሲያስፈልግ ተጨማሪ ራም አገጥማለሁ። የኃይል አቅርቦት ሲያስፈልገው እቀይርለታለሁ" ይላል።
ከትምህርት ውጭ ያለውን ፕሮግራም የሚመሩት ዳይሬክተር የኩዊንስ ከንቲባ ነበሩ። ከወላጆቹ ጋር ወደ ማዘጋጃ ቤት እንዲመጣ ጠየቁት፡፡
"ማዘጋጃ ቤት ስንደርስ ብዙ ኮምፒውተሮችን አሳየችን። ምናልባት 100 የሚሆኑ ኮምፒውተሮች ተከማችተው 'እነዚህ ኮምፒውተሮች እንዲጠገኑ እፈልጋለሁ' አለች፡፡"
ከዚያን ጊዜ አንስቶ ፍሬዲ ይህን የኮምፒውተር ክምር ለማስተካከል በየቀኑ በሰዓት 12 ዶላር እየተከለፈለው ጊዜውን ያሳልፍ ጀመረ።
"በእውነቱ የገንዘብ ጉዳይ አልነበረም፡፡ መሥራት የምፈልገውን ነገር የማድረግ ዕድል ነበረኝ። እናም ለእኔ በጣም አስደሳች ነበር፡፡"
ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ የኮዲንግ ዕድል ተፈጠረ፡፡ የኩዊንስ ከተማን የውሃ ግፊት መለኪያዎች ለመፈተሽ የሚያስችል ሥርዓት ያስፈልግ ስለነበረ አንድ ኩባንያ የኮምፒተር ፕሮግራም ለመሥራት 600,000 ዶላር አዘጋጀ፡፡
የከተማው ሥራ አስኪያጅ "ፍሬዲ ኮምፒውተር ስለሚያውቅ በዚህ ሊረዳ ይችል ይሆናል" ብለው እንደጠሩት ፍሬዲ ያስታውሳል
"ጌታዬ ይስሙኝ! ዕድል ከሰጡኝ ተመሳሳይ ፕሮግራም መሥራት እችላለሁ አልኩ። ያንን ፕሮግራም በሚፈልጉት መሠረት አዘጋጀሁ፡፡ 600,000 ዶላር አልተከፈለኝም፡፡ መደበኛ የደመወዝ ክፍያዬን አግኝቼ ወደ ቤት ተመለስኩ፡፡"
ይህ በፍሬዲ ሕይወት ውስጥ ወሳኝ የለውጥ ወቅት ነበር፡፡ 15 ዓመቱ ነበር። ትምህርቱን አቋርጦ የራሱን የኮምፒውተር ሥራ ለመጀመር ወሰነ። ለወላጆቹ በጣም አስጨናቂ ነበር፡፡
"እነሱ በትምህርት፣ በሥራ ፣ በጡረታ የሚያምኑ ስለሆነ ያንን ሰንሰለት ማቋረጥ ፈለኩኝ። የተለየ ነገር ለማድረግም ተነሳሁ" ይላል፡፡
አልዛይመር ያነሳሳው ፈጠራ
የፍሬዲ ንግድ ከጥንካሬ ወደ ጥንካሬ እየሄደ ሳለ ነበር የናታን የአልዛይመር በሽታ በፍጥነት የተባባሰው፡፡
ናታንን አንድ የሚረብሸው ነገር ሌሊት ከእንቅልፉ ሲነቃ ምሽት ላይ በቴሌቪዥን ያያቸውን ነገሮች እንደገና መሥራቱ ነው፡፡
ይህንን "በእኔ ላይ የደረሰብኝ በጣም አስደንጋጩ ነገር" ሲል ፍሬዲ ይገልጸዋል፡፡
"አንድ ቀን ጠዋት ሁለት ሰዓት ገደማ ነበር። አባቴ 'ገንስሞክ' ፊልምን ይወደው ነበርና ወደ መኝታ ቤቴ ገብቶ ዋና ገጸ ባህሪው ማት ዲሎን ነኝ ብሎ አሰበ፡፡ ጠመንጃ ይዞ ነበር፡፡ ከከተማ እንድትወጡ እፈልጋለሁ አለኝ።"
ፍሬዲ በወቅቱ "ትንሽ ጠብ" እንደነበረ ይናገራል። ጠመንጃውን ከአባቱ እጅ ነጥቆ ወደ አልጋው መልሶ አስተኛው፡፡
ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነቃ ግን ናታን ሄዷል፡፡
ይህ የአልዛይመር ምልክት ነበር። መሰል ነገር ከዚያ በፊትም ተከስቶ ነበር፡፡ ሁሌም ጫማውን ቢጫማም አንዳንዴ ሙሉ ለሙሉ ሳይለብስ ይወጣል።
ሁኔታው ፍሬዲ የመጀመሪያውን ትርፋማ የፈጠራ ሥራ እንዲጀምር ገፋፋው፡፡
ፍሬዲ "ስለዚህ የአባቴን ጫማ አነሳሁ። የጫማውን ሶል ቆረጥኩት። ቦርድ ሰርቼ በ90 ሜጋኸርዝ ድምጽ ማጉያ፣ ማይክራፎን እና ባለ ገመድ የአውታር መረብ ካርድ ጫማው ውስጥ አስቀመጥኩ" ብሏል፡፡
"ያንን ከላፕቶፔ ጋር አጣመርኩት። ይህ የአፕል ወይም የጉግል ካርታዎች ከመጀመራቸው በፊት ነበር። ያንን በቶምቶም እና በጋርሚን በኩል አጣምሬዋለሁ፡፡"
"አባቴ ከቤት ሊወጣ ይችላል። የላፕቶፔን አንድ ቁልፍ ተጭኜ 'ሠላም አባዬ የት ነህ?' እላለሁ፡፡ በጫማው ላይ ከድምፅ ማጉያ ሲሰማ እሱም 'ፍሬዲ የት እንዳለሁ አላውቅም!' ይል ነበር፡፡"
ከዚያ ፍሬዲ፤ ናታን ያለበትን ቦታ በጂፒኤስ ተከታትሎ ያገኘዋል። ይህንን ወደ ስምንት ጊዜ ማድረጉን ያስታውሳል፡፡
የናታን ጤንነት ይበልጥ ሲባባስ አንዳንድ የቤተሰቡ አባላት ወደ አረጋውያን መንከባከቢያ ቤት እንዲገባ ቢፈልጉም ፍሬዲ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ይልቁንም አባቱን ወደ ቢዝነስ ስብሰባዎች ወሰደው፡፡
"እሱ አልተወኝም። ስለዚህ እኔም አልተወውም" ይላል፡፡
ደንበኞችን ሲጎበኝ ናታንን በመኪናው የኋላ ወንበር ላይ አየር ማቀዝቀዣውን ከፍቶ፣ በሬዲዮ እንዲጫወት በሩን ቆልፎ ይተወው ነበር፡፡
"አንድ ጊዜ ስብሰባ ውስጥ ሆኜ በመስኮት ስመለከት አባቴ የኋላ መስኮቱን ከፍቶ ወደ ውጭ ወጣ። በፍርሃት ስሜት ውስጥ ነበርኩ። አሳፋሪ ነበር። 'መሄድ አለብኝ' አልኳቸው።"
ፍሬዲ ስብሰባውን አቋርጦ ወጣ። አባቱን በአቅራቢያው በሚገኝ የመኪና ማቆሚያ ማግኘቱ እፎይታ ሰጠው፡፡
እአአ ጥር 2014 ናታን በ81 ዓመቱ ሲያርፍ ፍሬዲ 24 ዓመቱ ነበር፡፡
"በእውነቱ ሰብሮኛል። ምክንያቱም ማድረግ የምፈልገው አባቴን ማስደሰት ብቻ ነበር፡፡"
"ጥሩ መሥራት እና በምችለው ሁሉ መርዳት እፈልጋለሁ"
ፍሬዲ የጫማ ዱካ መፈለጊያ የፈጠራ ሥራውን በ2.2 ሚሊየን ዶላር በመሸጥ ገንዘቡ እስኪገባለት ሲጠብቅ ቆየ፡፡
ናታን ሁልጊዜም የ1993 ፎርድ ፒክ አፕ መኪና እና የአሳ ማጥመጃ ጀልባ ባለቤት መሆን ይፈልግ ነበር። ፍሬዲ ይህን ለመግዛት አቅም ቢኖረውም ግን ዘግይቷል፡፡
ፍሬዲ "ሁኔታው በእውነት ዓይኖቼን ከፍቶልኛል። ገንዘብ ከመጠቀሚያነት ባለፈ ምንም እንዳልሆነ አስተምሮኛል። እናም ከማለፌ በፊት ዓለም የተሻለች እንድትሆን ለማድረግ በቻልኩት ሁሉ እሠራለሁ" ይላል።
"አባቴ በጭራሽ ሀብታም አልነበረም። ነገር ግን በብዙ ሰዎች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። እናም ላገኘኋቸው ሰዎች ሁሉ ጥሩ መሥራት እና በምችለው ሁሉ መርዳት እፈልጋለሁ፡፡"
ፍሬዲ ሌላ ምርጥ ፈጠራ አዘጋጀ። ይህም ከግል ተሞክሮው የተጨለፈ ነው። የእናቱን አጎት ለመጠየቅ የስምንት ዓመት ልጅ እያለ ጆርጂያን ጎበኘ፡፡
ፍሬዲ "ቤቱ ስንደርስ እናቴ እና አባቴ የቤቱን በር እያንኳኩ ነበር። ግን ማንም አልከፈተልንም" ይላል፡፡ "ስለዚህ አባቴ 'ስማ ፍሬዲ በመስኮቱ በኩል ገብተህ ዋናውን በርን መክፈት ትችላለህ?' " እንዳለው ያስታውሳል።
ፍሬዲ ገብቶ በሩን ከፈተ፡፡ ዘመዱ የእሳት ምድጃ አጠገብ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሁሉም ነገር ሠላም ነው ብሎ ያስብ ነበር፡፡
"አባቴ ወደ እሱ ሄደና እናቴን ጠርቶ 'ቤቲ ማይ ሕይወቱ አልፏል' ሲል ቃላቶቹን አስታውሳለሁ፡፡"
የፍሬዲ ዘመድ በስኳር ህመም ኮማ ውስጥ ሆኖ ሕይወቱ አለፈ፡፡
"የስኳር ህሙማን የደም ስኳራቸውን ሲፈትሹ መጻፍ አለባቸው። የእናቴ አጎት የስኳር መጠኑን ቢጽፈውም ገጠር ስለሚኖር የሚያይለት ሰው አልነበረም" ይላል ፍሬዲ፡፡
ስለዚህ ፍሬዲ በ22 ዓመቱ የሰውን የደም ስኳር መጠን ከቅርብ ዘመድ ጋር በፍጥነት የሚጋራ እና ንባቡን ዶክተር ሊያየው በሚችል የኤሌክትሮኒክ የጤና መዝገብ ላይ የሚያሰፍር ዘመናዊ ግሉኮሜትር ሠራ፡፡ በአንድ ሰው ደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ያልተለመደ ከሆነ ማስጠንቀቂያ ይልካል።
ፍሬዲ በትልቅ ፕሮጀክት ላይ መሥራትም ጀመረ፡፡ በብዙ የአሜሪካ የገጠር ክፍሎች የ 2ጂ ወይም የ 3ጂ በይነ መረብ እንደሌላቸው ያውቅ ነበር፡፡
ወደ እነዚህ የገጠር አካባቢዎች ዘመናዊ የኮሙኒኬሽን ዘዴዎችን ለማምጣት ፈለገ። እናም እአአ በ2008 የራሱን የቴሌኮም ኩባንያ ለማቋቋም ከፌዴራል ኮሙኒኬሽን ኮሚሽን ፈቃድ ጠየቀ።
"ትልልቅ የቴሌኮም አቅራቢዎች ከ1000 የማይበልጥ የሕዝብ ብዛት ባላቸው የገጠር አካባቢዎች ገብተው መሠረተ ልማታቸውን ኢንቨስት እንደማያደርጉ ማሳየት ነበረብኝ፡፡"
ቀላል ግን አልነበረም፡፡ 394 ሙከራ እና እጅግ ብዙ ገንዘብም ፈጅቷል፡፡
እአአ በ2011 የ21 ዓመቱ ፍሬዲ በአሜሪካ ትንሹ የቴሌኮም ኦፕሬተር ለመሆን በቃ፡፡ እንደ ኤንቢሲ ኒውስ ዘገባ ከሆነ ፊገርስ ኮሙኒኬሽንስ በአገሪቱ በጥቁር ባለቤትነት የተያዘ ብቸኛው የቴሌኮሙኒኬሽን ኩባንያ ነው፡፡
በመጀመሪያዎቹ ቀናት ፍሬዲ አብዛኛውን ሥራ ራሱ ነው የሚያከናውነው። ከመጀመሪያው የሞባይል ስልክ ማማ ኮንክሪት ጀምሮ እስከ ፋይበር ኦፕቲክ ኬብሎች ዝርጋታ ድረስ፡፡
በሰሜን ፍሎሪዳ እና በደቡባዊ ጆርጂያ በሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች አገልግሎት መስጠት ጀመረ። ኩባንያው ያለማቋረጥም አድጓል፡፡
እአአ በ2014 ፍሬዲ 'ፊገርስ ኤፍ1' የሚባለውን ጀመረ። እንቅስቃሴን በመለየት እና ከ10 ሜትር በሰዓት በላይ ሲሆን ስልክ መልዕክትም ሆነ ጥሪ እንዳይቀበል የሚያደርግ አሠራር ነው።
እአአ በ2019 ለሽያጭ የቀረበው ፊገርስ ኤፍ3 ስልክ በአምስት ሜትር ክልል ውስጥ በሽቦ አልባ መንገድ ባትሪውን ለመሙላት ያስችላል።
የኤፍ3 ግብይት ውዝግብ አስነስቷል። አንዳንድ ጦማሪያን የመጀመሪያ ገጽታዎችን በሙሉ አልያዘም ብለው ይከራከራሉ፡፡
ፍሬዲ ለቢቢሲ "ግባችን ጥራት ያለውና ዘመናዊ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረብን ሃቀኛ እና ግልጽ አገልግሎት መስጠት ነው" ብሏል፡፡
የ83 ዓመቷ የፍሬዲ እናትም የአልዛይመር በሽታ ጀምሯታል። ባገኘው ነገር በጣም እንደምትኮራ ይናገራል። የአጎቷን ሕይወት ሊያድን ይችል ለነበረው ግሉኮሜትር ፈጠራው "ልዩ እይታ" አላት ይላል፡፡
ፍሬዲ እአአ በ2015 ጠበቃዋን ናቲሊ ፊገርን አገባ። አንዲት ትንሽ ልጅም አላቸው፡፡
ከሥራው ጎን ለጎን በትምህርት እና በጤና እንክብካቤ ፕሮጄክቶች ላይ ኢንቨስት የሚያደርግ እና አቅመ ደካማ ልጆችን እና ቤተሰቦችን የሚረዳ ፋውንዴሽን ያስተባብራል።
የቅርብ ጊዜ ዕቅዱ በእንክብካቤ ማዕከላት ላሉ ብስክሌቶችን መስጠት እና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ለጤና ባለሙያዎች መከላከያ አልባሳትን መለገስን ያካትታል፡፡
ፍሬዲ ለትንሽ ልጁ ስለ ሕይወት የሚሰጣት በጣም አስፈላጊ ምክር "ዓለም ምንም ያህል ቀዝቃዛ ብትመስልም ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጪ" ነው።
በተጨማሪም በምታገኛቸው ሰዎች ሕይወት ሁሉ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማሳደር መሞከር እንዳለባት ይናገራል፡፡
የፍሬዲ አባት እና ቁጥር አንድ ደጋፊው ናታን ሙሉ በሙሉ የሚስማሙበት መልዕክት ነው።