ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር በምስጢራዊ ሠርግ መሞሸራቸው ተነገረ
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከእጮኛቸው ኬሪ ሲሞንድስ ጋር ምስጢራዊ በሆነ ሠርግ መጋባታቸው ተዘገበ።
የሠርጉ ሥነ ሥርዓት የተፈፀመው በትናንትናው ዕለት በዌስት ሚኒስተር ካቴድራል ሲሆን መታደምም የቻሉት ቤተሰቦችና የቅርብ ጓደኞች መሆናቸውንም በርካታ የአገሪቱ ጋዜጦች ዘግበዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በዚህ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።
የሥራና የጡረታ ሚኒስትር ፀሐፊ ቴሬሴ ኮፊ በበኩላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት "ቦሪስ ጆንሰንና ኬሪ ሲሞንድ ለዛሬዋ የጋብቻ እለታችሁ በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ" ብለዋል በትናንትናው ዕለት።
የሰሜን አየርላንድ መሪ አርሊን ፎስተር የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
ሜይል ኦን ሰንደይ እንደዘገበው የእንግሊዝ የኮቪድ-19 መመሪያ በሚያዘው መሰረት 30 የሚሆኑ እንግዶች ለሠርጉ ተጋብዘዋል ብሏል።
በሠርግ ዝግጅቱም ላይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች እንደተሳተፉበትና ሠርጉንም የመሩት ዳንኡል ሀምፍሬይስ የተባሉ ቄስ ናቸው ተብሏል።
ዘ ሰን የተባለው ጋዜጣ በበኩሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ስለሠርጉ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ነው የገለጸው።
የዌስት ሚኒስትር ካቴድራል ምዕመናን ከ7፡30 በፊት ከቤተ ክርስቲያኗ እንዲወጡ መነገራቸውንም ዘ ሰን አስነብቧል።
የ33 ዓመቷ ኬሪ ነጭ ጋወን ለብሳ በሊሞዚን ቤተ ክርስቲያን እንደደረሰችም ተዘግቧል።
የ56 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንና ኬሪ የፍቅር ግንኙነት እንዳላቸው በሚዲያዎች የተዘገበው ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር።
በቀጣዩ ዓመትም ቀለበት ማሰራቸውንና እርሷም ነፍሰጡር መሆኗን ገለፁ።
ልጃቸውም ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ነበር የተወለደው።