ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በካሊፎርኒያ የባቡር መንገድ ሰራተኛው ስምንት የስራ ባልደረቦቹን ገደለ
በካሊፎርኒያ አንድ የባቡር ሰራተኛ በማእከሉ የሚገኙ ስምንት የስራ ባልደረቦቹን ከገደለ በኋላ ራሱን እንዳጠፋ ተገልጿል።
ተኩሱ የተፈፀመው በሳንጆሴ ሳንታ ክላራ ቫሊ ትራንስፖርት ባለስልጣን መስሪያ ቤት ነው።
"ምክትል ኃላፊው በበር ወጥተው ሲያዩ ግለሰቡ እየተኮሰ ነበር" በማለት የክላራ ግዛት ፖሊስ ላውሪ ስሚዝ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ታጣቂው ረቡዕ ጥዋት በባቡር ጣቢያው ተኩስ የከፈተው በሰራተኞች ስብሰባ ላይ መሆኑን የሲቢኤስ ሚዲያ ዘግቧል።
የህግ አስከባሪዎችን ዋቢ አድርጎ ሲቢኤስ እንደዘገበው ገዳዩ የ57 አመቱ ሳሙኤል ካሲዲ የሚባል ግለሰብ ነው።
የቀድሞ ባለቤቱ ሲሲሊያ ኔልምስ ለኤፒ የዜና ወኪል እንደተናገረችው ካሲዲ የስራ ባልደረቦቹን መግደል ይፈልግ እንደነበርና ነገር ግን ሁኔታውን አላመንኩትም ነበር ብላለች።
የገዳዩ ጎረቤት ዶግ ሱህ ለሜርኩሪ የዜና ወኪል እንደተናገረው ታጣቂው "ብቸኛና ለዬት" ያለ ሰው ነበር ብሏል።
የሳንታ ክላራ ግዛት የፖሊስ ዲፓርትመንት ምክትል ቃለ አቀባይ ረስል ዴቪስ እንዳሉት ፖሊስ ከተጠርጣሪው ጋር የተኩስ ልውውጥ እንዳልተደረገ ነው።
ተኩሱ ከመከፈቱ በፊት የካሲዲ ቤት በእሳት መቃጠሉን የአካባቢው ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ታጣቂው ቤቱን በእሳት አቃጥሎ ተኩሱን ሳይከፍት አልቀረም የሚል ጥርጣሬዎች ባለስልጣናቱ አላቸው።
የሳንታ ክላራ የትራንስፖርት ባለስልጣን ሶስት የባቡር ጣቢያዎችን በበላይነት የሚቆጣጠር ሲሆን ይህም 65 ኪሎሜትር ይሸፍናል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ 70 የከተማ አውቶብሶችንም በበላይነት ያስተዳድራል።
የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ጋቪኡን ኒውሶም ሁኔታውን አውግዘው እንዲህ አይነት የጅምላ ግድያዎች አሰቃቂነትም ጠቅሰዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን "አሰቃቂ አደጋ" ያሉት ሲሆን ሰንደቅ አላማም ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አዘዋል።