ኢራን: ሁለቱ ወግ አጥባቂ ኢራናዊያን በሚቀጥለው ወር ምርጫ ለመሳተፍ ተመዘገቡ

ታትሟል

የኢራን ፍርድ ቤት ኃላፊ ኢብራሂም ራይሲ እንዲሁም የቀድሞው የፓርላማ አፈ ጉባዔ አሊ ላሪጃኒ በሚቀጥለው ወር ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለመሳተፍ ተመዝግበዋል።

ከጠቅላይ ገዢው አያቶላህ አሊ ካምኒ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው ሁለት ወግ አጥባቂዎች ሃሳን ሩሃኒን ለመተካት ከታጩት መካከል ቀደምት ናቸው ተብሏል።

ለዘብ ያለ አቋም ያላቸው ናቸው የሚባሉት ሩሃኒ ለሶስተኛ ጊዜ መወዳደር አይችሉም።

ለቀጣዩ ወር ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ከ300 በላይ ሰዎች በዕጩነት የተመዘገቡ ሲሆን መጀመሪያ ግን የጋርዲያን ካውንስልን ይሁንታ ማግኘት አለባቸው።

12 የካውንስሉ የኃይማኖት መሪዎችና ሕግ አዋቂዎች ባለፈው ምርጫ 1600 ሰዎች ተመዝግበው ስድስት ሰዎችን ብቻ መመልመላቸው ይታወሳል።

በፈረንጆቹ 2017 በተካሄደው በዚህ ምርጫ የመጀመሪያውን ዙር ሩሃኒ በ57 በመቶ ሲያሸንፉ ራይሲ 38 በመቶ አምጥተው ሁለተኛ መውጣታቸው አይዘነጋም።

ከዚህ ምርጫ በኋላ በኢራን የምጣኔ ሃብት ቀውስ ተከስቷል። የቀድሞው የአሜሪካ መሪ ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ ዳግም ማዕቀብ እንዲጣል ማድረጋቸው የሃገሪቱን ምጣኔ ሃብት ቀውስ አባብሶታል።

ትራምፕ፤ ኢራን ኒውክሊዬር ማብላላቷን ገታ ልታደርግ አሜሪካ ደግሞ ማዕቀቡን እንድታነሳ ሩሃኒ የገቡትን ስምምነት ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።

"በዚህ ምርጫ ላይ ራሴን ወክዬ በላይኛው የመንግሥት አካል ላይ ለውጥ ለማምጣት፣ ድህነትን ለመወጋት፣ ሙስናን ለማጥፋት እንዲሁም ውርደትና መገለልን ለመታገል መጥቻለሁ" ብለዋል የ60 ዓመቱ ራይሲ ለዕጩነት በተመዘገቡበት ወቅት።

ሰውዬው አክለው ከሩሃኒ ጋር ቅርበት አላቸው የሚባሉት ላሪጃኒን "ከአሁኑ ሁኔታ ጋር ቅርርብ የፈጠሩ ሰዎች ለውጥ እናመጣለን ሊሉ አይችሉም" ሲሉ በነገር ወጋ አድርገዋቸዋል።

የለውጥ አራማጆችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግን ሰውዬው በፈረንጆቹ 1988 በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እሥረኞችን በጅምላ እንዲገደሉ አድርገዋል በማለት ያላቸውን ስጋት ያነሳሉ።

ወግ አጥባቂው ዕጩ ግን በወቅቱ ሟቹ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ሩሆላህ ኮሚኒ ውሳኔ ስለሰጠቡት ግድያው ትክክል ነበር ይላሉ።

የ63 ዓመቱ ላሪጃኒ በበኩላቸው የቀድሞው የኒውክሌር ተደርዳሪ ነበሩ። አሁን ደግሞ የአያቶላህ ካሚኒ አማካሪ ናቸው።

ላሪጃኒ፤ ሌሎቹ ዕጩዎች በተለይ ደግሞ የፍትህና ወታደራዊ ልምድ ያላቸው ዕጩዎች የሃገሪቱን ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ መፍታት አይችሉም ይላሉ።

በሚቀጥለው ወር ምርጫ ለመሳተፍ ከተመዘገቡት መካከል ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት ኢሻቅ ጃሃንጊሪ እና የኒውክሌር ተደራዳሪው ሳዒድ ጃሊሊ ይገኑበታል።

ጋርዲያን ካውንሰሉ ይሁንታ ያገኙ ዕጨዑዎችን ዝርዝር ከ11 ቀናት በኋላ ይፋ ያደርጋል።