የስዊዟ ነባር ዲፕሎማት ኢራን ውስጥ ከፎቅ ወድቀው ሞቱ

ታትሟል

ቴህራን የሚገኘው የስዊዝ ኤምባሲ ነባር ሠራተኞ የሆኑት ዲፕሎማት ከመኖሪያ ቤታቸው ፎቅ ላይ ወድቀው መሞታቸውን የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የኢራን አደጋ ጊዜ አገልግሎት ቃል አቀባይ ለመህር ዜና ወኪል እንደተናገሩት የ51 ዓመቷ ዲፕሎማት 8 ፎቆች ካሉት ሕንፃ ላይ ነው ወድቀው የሞቱት።

ቃል አቀባዩ ዲፕሎማቷ በኤምባሲው ውስጥ ዋና ፀሐፊ ናቸው ቢሉም ስማቸውን ከመግለፅ ተቆጥበዋል።

የካምራኒዬህ አካባቢ ፖሊስ ሴትዬዋ ከወደቁ በኋላ የድንገተኛ ሕክምና ሰዎችን ቢጠሩም ሕይወታቸው አልፎ ነበር ብለዋል ቃለ አቀባዩ።

የስዊዝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኛው በአደጋ ምክንያት እንደሞቱበት ይፋ አድርጓል።

"የፌዴራል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እንዲሁም ኃላፊው ፌዴራል ካውንስለር ኢጋንዚዮ ካሲስ በድንገተኛው ሞት ክፉኛ ደንግጠዋል። ለሟች ቤተሰብ ሐዘናቸውንም ገልፀዋል" ብለዋል የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ከሟች ቤተሰቦችና ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ ይፋ አድርጓል።

ነገር ግን መረጃ ጥበቃና ግላዊ መረጃን አሳልፎ አለመስጠትን በመጥቀስ ስለ ዲፕሎማቷ አሟሟት ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዲፕሎማቷ ሞት የተሰማውን ሐዘን ገልጿል ሲል የሃገሪቱ ዜና ወኪል ኢርና ዘግቧል።

አክሎም የዲፕሎማቷ ሞት ምክንያት ምርመራ እየተደረገበት እንደሆነና ውጤቱ በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆንም አሳውቋል።

ኢርና የአደጋ ጊዜ አግልግሎትን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው የሴትዬዋ ሞት ራስ ማጥፋት አይደለም።

ስዊትዘርላንድ ኢራን ውስጥ የዩናይትድ ስቴትስን ዲፕሎማሲያዊ ፍላጎት በማንፀባረቅ ትታወቃለች። አሜሪካና ኢራን ከ1979 ኢስላሚክ አብዮት በኋላ ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የላቸውም።