ኤለን ዲጄነረስ ከ19 ዓመታት በኋላ የቴሌቪዥን ፕሮግራሟን ልታቋርጥ ነው

ታትሟል

አሜሪካዊቷ ጉምቱ የቴሊቪዥን 'ሾው' አቅራቢ ኤለን ዲጄነረስ ለበርካታ ዓመታት ስትመራው የነበረውን ተወዳጅ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ልታቋርጥ መሆኗን ይፋ አድርጋለች።

"ቀጣዩ ዓመት የመጨረሻው እንዲሆን እሻለሁ" ብላለች ኤለን ውሳኔውን ስታሳውቅ።

ባለፈው ዓመት በስሯ ያሉ ሰዎች የሥራ ቦታ ምቹ አይደለም ሲሉ ስላቀረቡት ክስ በቀጥታ ያለችው ነገር የለም።

ከዚህ ወቀሳ በኋላ ሶስት የዝግጅቱ ነባር አዘጋጆች ሥራቸውን የለቀቁ ሲሆን ኤለንም በቴሌቪዥን ቀርባ ይቅርታ ጠይቃ ነበር።

የ63 ዓመቷ ኤለን ለ19 ዓመታት የታየውን የቴሌቪዥን ሾው በ2022 ለመቋጨት ማሰቧን ሹክ ያለችው ወቀሳው ከመሰማቱ በፊት ነበር።

"ከሁለት ዓመት በፊት ለሶስት ዓመታት የሚቆይ ፊርማ ፈርሜ ነበር። ሁሌም ውስጤ የሚነግረኝ 19ኛው ዓመት [ሲዝን 19] የመጨረሻዬ እንደሚሆን ነው" ስትል ሐሙስ ዕለት በሚተላለፈው ፕሮግራሟ መግቢያ ላይ እንደምትናገር ከማስታወቂያው መስማት ተችሏል።

ዘ ኤለን ዲጄነረስ ሾው በአውሮፓውያኑ ከመስከረም 2003 ጀምሮ የተላለፈ ሲሆን 3 ሺህ ክፍሎች ታይተዋል።

በዝግጅቱ ወቅታዊ የሆኑ ቀልዶች፣ ቃለ ምልልሶች እንዲሁም ቀልብ የሚስቡ ታሪኮች ተላልፈውበታል።

ምንም እንኳ የፕሮግራሙ ተቀባይነት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየቀዘቀዘ ቢመጣም በርካታ ተመልካቾችን በአሜሪካና በመላው ዓለም ማፍራት የቻለ ነው።

ኤለን ሐሙስ ምሽት በሚተላለፈው ክፍል ታዋቂዋ የሙያ አጋሯ ኦፕራ ዊንፍሬይን እንግዳ አድርጋ ታቀርባለች።

ኤለን ዲጄነረስ በ1990ዎቹ በሠራቻቸው ስታንድ አፕ ኮመዲዎች ነው ወደ ዝና ጣራ የወጣችው።

ኤለን ዲጄነረስ ሾው 60 ጊዜ ኤሚ ለተሰኘው ሽልማት የታጨ ሲሆን በቅርቡ የ2020 ምርጥ የመዝናኝ ቶክ ሾው ተብሎ ታጭቶ ነበር።