ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከንቲባው በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ ቢባሉም ከእስር ቤት ማስተዳደራቸው ቁጣን ፈጠረ
"በቀላሉ መገመት ትችላላችሁ። ፍርድ ቤቱ በሚወስነው ጉዳይ ሚዛናዊነት በተሞላው መልኩ አስተያየት ልሰጥ የምችል ዋነኛ ሰው አይደለሁም" የሚለው አረፍተ ነገር በፈረንሳይዋ ከተማ ድራቬይል ምክር ቤት የሚወጣው መፅሄት ርዕሰ አንቀፅ መግቢያ ነው።
ይህንን የፃፉት የከተማዋ የቀድሞ ከንቲባና በቅርቡ በመድፈርና ጥቃቶችን በማድረስ ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው የተገኙት የ63 አመቱ ግለሰብ ናቸው።
ምንም እንኳን ግለሰቡ ጥፋተኛ ተብለው ማረሚያ ቤት ቢሆኑም በቅርቡ የተደረገው ይግባኝ ጆርጅስ ትሮን ከእስር ቤት ሆነው ከተማዋን እንዲያስተዳድሩ ፈቅዶላቸዋል።
በርካቶች በዚህ የተነሳ ቁጣቸውን እያሰሙ ነው።
በያዝነው ሳምነት ማክሰኞ በከተማዋ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በዚህችው በፓሪስ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው ከተማ ከንቲባው ከስልጣን እንዲወገዱ ጠይቀዋል። የከንቲባውን በስልጣን መቆየት በመቃወም ድምፃቸውን አሰምተዋል።
ሜምበርስ ኦፍ ዘ ኖት ኢን ድሬቬይል ኦር ኤኒ ዌር ኤልስ የተባለው ቡድን አባላት የተቃውሞ ሰልፉ ላይ እንደ ዶሮዎች በመልበስ የአካባቢውን ፖለቲከኞች "ቦቅቧቆች ናችሁ" ሲሉ ዘልፈዋቸዋል።
ከንቲባ ትሮን እስር ቤት የወረዱበት ጉዳይ የተጀመረው ከአስር አመት በፊት ነው። በወቅቱ በሚኒስትርነት የስልጣን ቦታ ላይ የነበሩት ግለሰብ ሁለት የቀድሞ ሰራተኞቻቸውን ደፍረዋል እንዲሁም ጥቃቶች ፈፅመዋል በሚል ክስ ከስራ እንዲለቁ ተገደዱ።
በመጀመሪያ በነበረው የክስ ሂደት ነፃ ቢወጡም በዚህ አመት የካቲት ወር ላይ የአምስት አመት እስር ተፈረደባቸው። ከዚህም በተጨማሪ ለስድስት አመታት ያህልም በየትኛውም የመንግሥት ስልጣን ቦታ ላይ እንዳይቀመጡ ታገዱ።
ውሳኔው ይህ ከሆነ ከእስር ቤት ሆነው የማስተዳደራቸው ሁኔታ እንዴት ተፈጠረ ታዲያ?
ችግሩ የአካካቢው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ፍራንኮይስ ዳሜርቫል እንደሚሉት ትሮን በብያኔው ላይ ይግባኝ የጠየቁ ሲሆን ይህም ማለት የመጨረሻ ውሳኔ እስኪወሰን ድረስ ንፁህ እንደሆኑ ይቆጠራል።
በዚህም ሂደት መሰረት ከእስር ቤትም ሆነው የከንቲባ ኃላፊነታቸውንና ተግባራቸውን ይወጣሉ ማለት ነው።
የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ሚኒስትርና የከንቲባው የመጀመሪያ የፍርድ ሂደት ላይ ጠበቃ የነበሩት ግለሰብ ከዚህ ቀደም እንዳሉት መንግሥት ባለው የይግባኝ ሂደት ከንቲባው ከስልጣን ማንሳት እንደማይችል ነው።
"አሁን ያለው ስርዓት ከፍተኛ ችግር ያለበት ነው ምክንያቱም በመድፈር ወንጀል የተበየነባቸውን ግለሰቦችም ጥበቃ ያደርግላቸዋል። ምንም እንኳን ንፁህ ሆነው ሊገኙ ይችላሉ የሚለው እሳቤ እንዳለ ቢሆንም። ነገር ግን ከሁሉም በላይ ከንቲባው የማስተዳደር የሞራል ብቃት የለውም" በማለት ተቃዋሚ ፖለቲከኛው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
"በአሁኑ ወቅት ወረቀት ላይ ከንቲባ ቢሆንም ሰራተኞቹን በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ነው" ይላሉ።
የትሮን ተቃዋሚዎች ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ በዋነኝነት የሚያተኩሩትም የሚነሱ የሞራል ጥያቄዎች ላይ ነው።
ሌላኛው የአካባቢው ፖለቲከኛ ጋብርዬል ቦይሪ ቻርልስ በበኩላቸው በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ላይ የፈረንሳይ ምክር ቤት የከንቲባውን ስልጣን የመሻር መብት አለው ይላሉ።
"በዚህ ወቅት ላይ የሞራል የበላይነት ሊተገበር በተገባ ነበር ምክንያቱም ግለሰቡ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘበት ጉዳይ በከንቲባው በስልጣኑ ወቅት የተፈፀመ በመሆኑ ነው" ይላሉ።
ነገር ግን ከንቲባውን ከስልጣን ለማስወገድ የአካባቢውን ነዋሪ ሙሉ ድጋፍ ማግኘት እንደታሰበው ቀላል አልሆነም።
"የምንኖርባት ከተማ ትንሽና 30 ሺህ ህዝብ የሚኖርባት ናት። ከንቲባው በስልጣን ላይ ለሃያ አምስት አመታት ያህል መቆቱም የራሱን ስልጣን የሚያጠናክርበት ጠንካራ ስርዓት መዘርጋት አስችሎታል" ይላሉ ፖለቲከኛዋ
የካቲት ወር ላይ ከታሰሩ ጀምሮ ስራቸውን ያላቋረጡት ከንቲባ ትሮን የምክር ቤት ስብሰባዎችን ይካፈላሉ፤ መግለጫዎችንም በተወካዮቻቸው በኩል ፅፈው ይልካሉ።
ምክትላቸው ሪቻርድ ፕሪቫት ከንቲባው በእስር ላይ ሆነው ስራቸውን መቀጠላቸውን በተመለከተ እንደሚደግፋቸው ተናግረዋል።
ሪቻርድ ፕሪቫት ለፈረንሳይ ቴሌቪዥን በሚያዝያ ወር ላይ እንደተናገሩት "በአሁኑም ወቅት ከንቲባ ነው። ይህንን የሚያስቀይር ተፃራሪ ነገር እስካልመጣ ድረስ በዚሁ ይቀጥላል። ከከንቲባነቱ ያስወገደው አካል የለም ስለዚህ በከንቲባነቱ ይቀጥላል" ብለዋል።
በባለፈው ወር በነበረ የምክር ቤት ስብሰባ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ከንቲባው ከስልጣን እንዲወገዱ ጥያቄ ቢያቀርቡም የድምፅ መስጠት ስነ ስርአቱ ከመከናወኑ በፊት የከንቲባው ደጋፊዎች ስብሰባውን ረግጠው በመውጣታቸው ሳይከናወን ቀርቷል።
ቦይሪ ቻርልስ እንደሚሉት በበይነ መረብ የሚሰጡ ትችቶችና ውግዘቶችም እንዲታገዱ መደረጋቸውን ነው።
"በከተማው ምክር ቤት የፌስ ቡክ ገፅ ላይ ከንቲባው ከእስር ቤት ሆኖ የፃፈውን ነገር ያተሙት ሲሆን ተቃዋሚዎች ግን መፃፍ ፈልገው ታግደዋል። በከንቲባው ላይ አሉታዊ አስተያየት ወይም ትችት ከተሰጠ እንዲጠፋ ይደረጋል። በዚህ ከተማ ለክርክርና ለውይይት መድረክ የለውም" የሚሉት ፖለቲከኛዋ
"በአሁኑም ወቅት ከንቲባው የሞራል የበላይነት እንዳለው ለማሳየት ይሞክራል። በጉዳዩ ላይ የቀጠለው ዝምታ፣ ክህደትና ለከንቲባው የተሰጠው ድጋፍ እንደ ማህበረሰብ ያለንን ውድቀት ያሳያል" በማለት አክለዋል።
የከንቲባው ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ከስልጣን እንዲወርዱ አሁንም ግፊት እያደረጉ ነው። ከንቲባው እንዲለቁ የሚጠይቅ በበይነ መረብ የሚደረግ ፊርማ ላይ 35 ሺህ ሰዎች ፈርመዋል፥
ናዳ የተባለ ቡድን መስራች ከሆኑት አንዱ ራፋኤል ዲሞንቺ እንደሚሉት የተቃውሞ ሰልፎችን ከማድረግ በተጨማሪ ቡድኑ ከንቲባው ከስልጣን ለምን መወገድ እንዳለባቸው በተመለከተ ከማህበረሰቡ ጋር ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል።
"ይሄ ጉዳይ የድሬቬይል ትሮን ጉዳይ ብቻ አይደለም። አለም አቀፋዊ ሁኔታ ነው። የፈረንሳይ ሪፐብሊክ ከተመረጡ ባለስልጣናትን በተመለከተ የምትቀበለውም ነገር አሳይ ነው" ይላሉ።
"ከ'ሚቱ' ዘመን በኋላ እንዲህ አይነት ወሲባዊ ጥቃቶች የፈፀሙ ሰዎች ሳይቀጡ የሚታለፍበት መንገድ የለም" በማለት የሚናገሩት ዳሜርቫል "በዚህ ወቅት ግለሰቡ በእስር ቤት ሆኖ ማስተዳደሩም ለሴቶች ስድብ ነው" ብለዋል።