ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የላብ አደሮች ቀን ተቃውሞ በዓለም ዙሪያ ተፋፍሟል
የቱርክ ፖሊስ ከ200 በላይ በላብ አደሮች ቀን ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞችን በቁጥጥር ሥር አውሏል።
ምንም እንኳ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አሁንም ስጋት ቢሆንም በበርካታ የዓለማችን ከተሞች በርካቶች የላብ አደሮች ቀንን በማስታከክ ተቃውሞ ወጥተዋል።
በቱርክ ትልቋ ከተማ ኢስታንቡል የኮሮናቫይረስ ሕግጋትን የጣሱ ሰዎች አደባባይ ወጥተዋል።
በበርካታ ሃገራት ፖሊስ የኮሮናቫይረስ ሕግጋትን እንዲያስከብርና እነዚህን ሰልፎች እንዲበትን ተሰማርቶ ታይቷል።
የተቃውሞ ሰልፍ ካስተናገዱ ሃገራት መካከል ጀርመን፣ ሩስያ፣ ስፔን፣ ስዊድን፣ ዩኬ፣ ኮሎምቢያ፣ ፊሊፒንስና ኢንዶኔዥያ ይገኙበታል።
በበርካታ ከተሞች የተካሄዱት ብዙዎቹ ሰልፎች ሰላማዊ ነበሩ።
ነገር ግን በቱርክ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ወደ ብጥብጥ ተቀይሮ ፖሊስ በርካቶችን በቁጥጥር ሥር አውሏል።
የኢስታንቡል አስተዳደር ቢሮ እንዳለው ቢያንስ 212 ሰዎች ከተቃውሞ ሰልፍ ወጥተው ወደ ታስኪም አደባባይ ሊሄዱ በመሞከራቸው በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
የተቃውሞ ሰልፉን የሚያሳዩ ምስሎች ፖሊስ በመከላከያው ተቃዋሚዎችን ሲገፋ አንዳንዶችን ደግሞ ከሰልፈኞች ነጥሎ እየጎተተ ሲያስወጣ ያሳያሉ።
ቱርክ በፍጥነት እየተስፋፋ ያለውን ወረርሽኝ ለመቀነስ ወደ ሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ የገባችው ባለፈው ሳምንት ነበር።
በፈረንሳይ ደግሞ በዋና ከተማዋ ፓሪስ ቢያንስ 46 ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል።
አንዳንድ ተቃዋሚዎች ከአድማ በታኝ ፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል፤ ድንጋይ ወርውረዋል፤ የቆሻሻ መጣያዎችን አቃጥለዋል ተብለው ነው በቁጥጥር ሥር የዋሉት።
የፈረንሳይ መንግሥት አንድ የእሣት አደጋ ሠራተኛን ያጠቃ ተቃዋሚን ኮንኗል።
በፈረንሳይ ዙሪያ ቢያንስ 300 ሰልፎች የተዘጋጁ ሲሆን ከ106 ሺህ በላይ ሰልፈኞች አደባባይ ወጥተዋል ይላል ከሃገር ውስጥ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ።
ተቃዋሚዎቹ መንግሥት የሥር አጥ ዜጎችን ጥቅም ያስከብር፤ የምጣኔ ሃብት ፍትህ ያምጣ ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
ሰልፍ በሰላማዊ መንገድ በተጀመረባት በርሊን 10 ሺህ ብስክሌተኞች ፀረ-ካፒታሊስት ተቃውሞ አካሂደዋል። ነገር ግን አመሻሹን ተቃዋሚዎች እሣት በመለኮሳቸው ሰልፉ ወደ አመፅ ተቀይሮ ነበር።
በለንደንም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ውለዋል።
በየዓመቱ ሜይ 1 [በፈረንጆቹ] የሚከበረውን የዓለም ላብ አደሮች ቀንን በማስመልከት የሠራተኛ ማሕበራት ሰልፍ ያዘጋጃሉ።
በርካታ ሰዎችን ከሥራ ያፈናቀለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለዘንድሮው ዓመት ተቃውሞ ቤንዚን ሳይሆን አልቀረም።