ፕሬዝደንቱን "ደደብ" ብሎ የዘለፈው ፖላንዳዊ ፀሐፊ ተከሰሰ

ታትሟል

ታዋቂው ፖላንዳዊ ደራሲና ጋዜጠኛ ፕሬዝደንት አንድሬዝ ዱዳን "ደደብ" ብሎ በመሳደቡ ክስ ቀርቦበታል።

ባለፈው ኅዳር ፕሬዝደንቱን "ደደብ" ሲል በፌስቡክ ገፁ የዘለፈው ፀሐፊ እስከ ሶስት ዓመት እሥር ሊፈርድበት ይችላል ተብሏል።

ጃኮብ ዙልዚክ ፕሬዝደንት ዱዳን የዘለፋቸው የአሜሪካን የምርጫ አሠራር አላወቁም በማለት ነው።

ፕሬዝደንት ዱዳ ለጆ ባይደን እንኳን ደስ አለዎ ብለው በትዊተር ገፃቸው ላይ የለጠፉት "ለምርጫ ቅስቀሳዎ እንኳን ደስ አለዎ" በማለት ነበር።

ፖላንድ ውስጥ ባለሥልጣን አሊያም ኃይማኖት መዝለፍ ወንጀል ነው።

ዱዳ በትዊተር መልዕክታቸው "የኢሌክቶራል ኮሌጅ ምርጫን እስክናውቅ ድረስ ፖላንድ የሁለቱን ሃገራት የፀና ቁርኝት ወደፊትም ለማስቀጠል ቆርጣለች" ብለው ነበር።

ፀሐፊው በበኩሉ የአሜሪካን ፖለቲካ "ከራስ ፀጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ አጥንቻለሁ፤ የኢልክቶራል ኮሌጅ ምርጫ የሚባል ነገር ግን ሰምቼ አላውቅም" ሲል ፅፏል።

ጃኮብ በፌስቡክ ገፁ "ጆ ባይደን 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ናቸው" ካለ በኋላ "ዱዳ ደግሞ ደደብ ናቸው" ሲል አክሏል።

አቃቤ ሕግ የፀሐፊው የፌስቡክ መልዕክት "አፀያፊ" እና "ተቀባይነት የሌለው" ነው ብሏል።

ጃኮብ ክስ እንደተመሠረተበት የሰማው ከመገናኛ ብዙሃን እንደሆነ ይናገራል።

በፖላንድ እጅግ ታዋቂ ፀሐፊ የሆነው ጃኮብ በፈረንጆቹ 2014 የፃፈው 'ብላይንድድ ባይ ዘ ላይትስ' የተሰኘው መፅሐፉ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን አትርፎለታል።

ይህ መፅሐፍ ኤችቢኦ አውሮፓ በተሰኘው የፊልም አሰራጭ ኩባንያ ተከታታይ ድራማ ሆኖ ለቴሌቪን እንዲቀርብ ተደርጓል።

ነገር ግን ይህ ዝናው ፕሬዝደንት ዱዳን ዘልፎ በነፃነት ከመራመድ ያተረፈው አይመስልም።

ፖላንድ ስድብን በተመለከተ ዘጠኝ ሕግጋት አሏት።

አንደኛው የሃገሪቱን ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንዲሁም ባንዲራን የመሳሰሉ ምልክቶችን የሚመለከት ሲሆን ሁሉንም ሕግጋት የተላለፈ እሥር ይጠብቀዋል።

2017 ላይ አውሮፓ ውስጥ ስም ማጥፋትና መዝለፍን በተመለከተ የትኛዋ ሃገር ጠበቅ ያለ ሕግ አላት የሚለውን ለመለየት የተሠራ ጥናት ፖላንድን ቁንጮ አድርጓታል።

ፖላንድ ውስጥ የሃገሪቱን ባንዲራ ብቻ ሳይሆን የሌሎች ሃገራትን ባንዲራም መዝለፍ ለእሥር ሊዳርግ ይችላል።