ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በመብት ጥሰት ምክንያት ቻይና በምዕራባውያን ማዕቀብ ተጣለባት
በርካታ የምዕራብ አገራት በሙስሊም የዊጋ አናሳ ቡድንን መብት ጥሳለች በሚል በቻይና በባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ ጣሉ።
ቻይና በሰሜን-ምዕራብ በዢንጂያንግ በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ዊጋዎች አስቀምጣለች። በካምፖቹ ውስጥ ስቃይ፣ አሰገዳጅ የጉልበት ሥራ እና ወሲባዊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል።
ማዕቀቦቹ የአውሮፓ ሕብረት፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ እና ካናዳ በጋራ የተቀናጀ ጥረት የተጣሉ ናቸው።
ለዚህም ቻይና በአውሮፓ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀቦች በመጣል ምላሽ ሰጥታለች።
መጠለያ ጣቢያዎቹ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚያገለግሉ የ"ተሃድሶ" ተቋማት መሆናቸውን በመግለፅ ክሶቹን አስተባብላለች።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ ግን የዊጋዎች አያያዝ "እጅግ መሠረታዊ የሆኑ የሰብአዊ መብቶችን የጣስ ነው" ብለዋል።
ቤጂንግ በሚገኘው በቲያናንሚን አደባባይ በአውሮፓውያኑ 1989 ዴሞክራሲ ይስፈን የሚሉ ሠልፈኞች ላይ የተኩስ እሩምታ መከፈቱን ተከትሎ ከጣለው ማዕቀብ በኋላ የአውሮፓ ሕብረት በቻይና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት አዲስ ማዕቀብ ሳይጥል ቆይቷል።
ስለ ማዕቀቡ ምን እናውቃለን?
በዊጋ ሙስሊሞች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸም የተከሰሱ የዢንጂያንግ ኃላፊዎች የጉዞ እቀባዎችን እና የንብረት እገዳ ተላልፎባቸዋል።
ዕገዳ የተጣለባቸውም፤
- ቼን ሚንጉዎ፡ በዢንጂያንግ የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ዳይሬክተር የአካባቢው የፖሊስ ኃይል
- ዋንግ ሚንግሻን፡ የአውሮፓ ሕብረት እንደሚለው የዢንጂያንግ የኮሚኒስት ፓርቲ ቋሚ ኮሚቴ አባል ሲሆኑ የዊጋዎችን መታሰርን "የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለው ቁልፍ የፖለቲካ አቋም ያላቸው" ናቸው።
- ዋንግ ጁንዤንግ፡ በመንግሥት ባለቤትነት የተያዘው የዢንጂያንግ ማምረቻ እና ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የፓርቲ ፀሐፊ ናቸው።
- ዡ ሃሉነ ፡ በዢንጂያንግ የቀድሞው የኮሚኒስት ፓርቲ ኃላፊ ሲሆኑ የ"ካምፖችን" እንቅስቃሴን በበላይነት በመቆጣጠር "ቁልፍ የፖለቲካ አቋም" በመያዛቸው ነው የተከሰሱት።
- የዢንጂያንግ ምርትና ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ
የዩናይትድ ኪንግደም የውች ጉዳይ ኃላፊ ዶምኒክ ራብ በዢንጃንግ ውስጥ በዊጋ ሙስሊሞች ላይ የሚደርሰውን በደል "በዘመናችን ካሉት እጅግ የከፋው የሰብዓዊ መብቶች ቀውሶች አንዱ" ሲሉ ጠርተውታል።
"ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለእንዲህ ዓይነቱ ከባድ እና ስልታዊ የመብት ጥሰቶች ፈጻሚዎች ተጠያቂ ለማድረግ በሕብረት አንሠራለን" ሲሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሰጡት መግለጫ ቻይና "የዘር ማጥፋት እና በሰው ልጆች ላይ ወንጀል እየፈፀመች ነው" ብለዋል።
አሜሪካ በዋንግ ጁንዤንግ እና ቼን ሚንጉዊ ላይ "ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማሰር እና ከባድ የአካል ጥቃት በማድረስ እንዲሁም ከሌሎች ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች" ጋር ባላቸው ግንኙነት ማዕቀብ እንደጣለች ገልጻለች።
የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበከሉላቸው "መረጃዎች የቻይና ባለሥልጣናት ስልታዊ እና በመንግሥት የሚመራ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደሚካሄዱ ያመለክታሉ" ብለዋል።
ማዕቀቡ የመጣው ቻይና በዊጋዎች ላይ ያላትን አያያዝ በተመለከተ ዓለም አቀፍ ምርመራ እየጨመረ መምጣቱን ተከለትሎ ነው።
ቻይና በምን ተከሰሰች?
ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዊጋች እና ሌሎች አናሳ ማኅበረሰቦች በዢንጂያንግ ውስጥ በሚገኙ ካምፖች እንደታሰሩ ይገመታል።
ዢንጂያንግ በሰሜን ምዕራብ ቻይና የሚገኝ ሲሆን የአገሪቱ ትልቁ ክልል ነው። እንደ ቲቤት ሁሉ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር ነው። ይህም ማለት በንድፈ ሀሳብ ደረጃ የተወሰነ የራስ-ማስተዳደር ስልጣኖች አሉት። በተግባር ግን በማዕከላዊው መንግሥት ከፍተኛ ገደቦችን ያርፉበታል።
በክልሉ ውስጥ የሚኖሩት ዊጋዎች የቱርክን የሚመሰል የራሳቸውን ቋንቋ ይናገራሉ። ራሳቸውንም ከባህል እና ከብሔር አንጻር ከመካከለኛው እስያ አገራት ጋር እንደሚቀራረቡ ይነገራል።
የቻይና መንግሥት የዊጋ ሴቶች በግዳጅ መካን እንዲሆኑ እና ህፃናትን ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው በመለየት ይከሰሳል።
በየካቲት ወር ይፋ በተደረገ የቢቢሲ ምርመራ ስልታዊ በሆነ መንገድ አስገድዶ መድፈር፣ ወሲባዊ ጥቃት እና እስረኞችን የማሰቃየት ተግባር እንደሚከናወን ከመጀመሪያ ደረጃ ምስክር አቅርቧል።
አንዲት ሴት "በየምሽቱ" ሴቶች ከታሰሩበት እንደተወሰዱ በአንድ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑና ጭምብል በለበሱ ቻይናውያን ወንዶች እንደሚደፈሩ መስክራለች። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በካምፑ በጥበቃ ሠራተኝነት ይሠሩ የነበሩ ግለሰብ እስረኞችን ማሰቃየት እና የምግብ እጦት እንዳለ ገልፀዋል።
ቻይና የቢቢሲ ወርልድ ኒውስ ቴሌቪዥንን በዊጋ ማልበረሰብና በኮሮናቫይረስን አዘጋገብ ምክንያት አግዳለች።
አገሪቱ መጀመሪያ ካምፖቹ አለመኖራቸውን ገለጸች ሲሆን በኋላ ደግሞ ሽብርተኝነት ለመከላከል አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን ጠቅሳለች። በሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ የተነሱ ክሶችንም አስተባብላለች።
ቻይና ለማዕቀቦቹ ምን ምላሽ ሰጠች?
በአውሮፓ ሕብረት ይፋ የተደረገው ማዕቀብ "በውሸት እና በውሸት መረጃ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው" ብላለች ቻይና።
በምላሹም የቻይናን ሉዓላዊነት እና ጥቅም በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዱ እንዲሁም የውሸት መረጃዎችን የሚያሰራጩ ያለቻቸውን 10 ሰዎች እና አራት ድርጅቶች ላይ ማዕቀብ እንደጣለች ገልጻለች። በቻይና ማዕቀብ ተጣለባቸው ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ወይም የንግድ ሥራ አብረው እንዳይሠሩ ታግደዋል።
የአውሮፓ ፓርላማ ልዑካን ሊቀመንበር የሆኑት ጀርመናዊው ፖለቲከኛ ሬንሃርድ ቡቲኮፈር የቻይና ማዕቀቡ ከተጣለባቸው ሰዎች መካከል ናቸው። በቻይና የዢንጂያንግ ፖሊሲ ባለሙያ የሆኑት አድሪያን ዜንዝ እና ስዊዲናዊው ምሁር ቦርን የርደንም ማዕቀቡ ይመለከታቸዋል።
ዊጋዎች በግዳጅ መካን እንዲሆኑ ይደረጋል የሚለው ሪፖርታቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲመረምረው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ እንዲያቀርብ ያስቻለ ነው። የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን "ፀረ-ቻይና" ሲሉ የሚገልጿቸው ሲሆን ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨትም ይከሷቸዋል።
በቻይና ማዕቀብ ከተጣለባቸው ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ሆላንዳዊው የሕግ ባለሙያ ሾየርድ ሾየርድስማ በበኩላቸው የቻይናን ውሳኔ "ጫናን መቋቋም እንደማትችል ማሳያ ነው" ብለውታል።
"ይህ ለሁሉም የአውሮፓውያን ባልደረቦቼ ማበረታቻ በመሆኑ ልንናገር ይገባል" ሲሉ በትዊተር ገጻቻው ላይ አስፍረዋል።