የዶናልድ ትራምፕ ሀብት በአያሌው አሽቆለቆለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀብታቸው በ700 ሚሊዮን ዶላር ቀንሶባቸዋል ሲል ብሉምበርግ ዘገበ።
አስገራሚው ነገር ሀብታቸው ያሽቆለቆለው ፕሬዝዳንት በሆኑባቸው ዘመናት መሆኑ ነው።
አሁን የሰውየው ድምር ሀብት 2.3 ቢሊዮን ብቻ ነው።
ለትራምፕ ሀብት መቀነስ ዋና ምክንያት ተደርጎ የተወሰደው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲሆን የትራምፕ እውቅ ሆቴሎች፣ ጎልፍ ክለቦችና መዝናኛ ማዕከላቱ በደንበኞች ድርቅ መመታታቸው 700 ሚሊዮን ዶላር አሳጥቷቸዋል።
ዶናልድ ትራምፕ አሁን ከቤተሰብ ቢዝነስና ከግብር ክፍያ ጋር በተያያዘ የወንጀል ምርመራ ፋይል ተከፍቶባቸዋል።
ብሉምበርግ የሰውየውን ወጪና ገቢ ከግንቦት 2016 ጀምሮ እስከ ጥር 2021 ድረስ ሲያሰላው ቆይቷል። ፕሬዝዳንቱ ነጩ ቤተ መንግሥት ከመግባታቸው በፊትና በኋላ የሀብታቸውን ከፍና ዝቅ አስልቶታል።
ትራምፕ የሀብታቸው ሦስት እጅ የሚይዘው የሪልስቴት ልማት ነው። ለቢሮ የሚውሉት የትራምፕ ፎቆች ገቢያቸው በከፍተኛ ሁኔታ ያሽቆለቆለ ሲሆን ይህም በወረርሽኙ ምክንያት ሰዎች ከቤታቸው መሥራት በመጀመራቸው የቢሮ አስፈላጊነት እየቀነሰ በመምጣቱ ነው።
የገንዘብና ሀብት ሰነዶችን በማውጣት የሚታወቀው ብሉምበርግ እንደሚለው የዶናልድ ትራምፕን ስምና የንግድ ምልክታቸውን በመሸጥ የሚተዳደሩና በቀጥታ በራሳቸው ሥር የተቋቋሙ 19 ጎልፍ መጫወጫ ሜዳዎች አሏቸው።
ከዚህ ሌላ 12 የሚሆኑ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ይገኛሉ።
ምንም እንኳ ጎልፍ ተራርቆ በመቆም የሚጫወቱት ስፖርት በመሆኑ በወረርሽኑ ጊዜ ተመራጭ ስፖርት ሆኖ ቢቀጥልም የዶናልድ ትራምፕ በስኮትላንድ የነበሯቸው ሁለት ዕውቅ የጎልፍ ሜዳዎች ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶባቸዋል።
በተለይም ነውጠኛ ደጋፊዎቻቸው ባለፈው ጥር ካፒቶል ሒልን መውረራቸውን ተከትሎ የአሜሪካ ፕሮፌሽናል ጎልፍ ተጫዋቾች ማኅበር በ2022 በኒው ጀርሲ በትራምፕ የጎልፍ ሜዳ ሊያዘጋጀው የነበረውን የጎልፍ ውድድር በመሰረዙ ትራምፕ ዳጎስ ያለ ትርፍ አምልጧቸዋል።
ትራምፕ በ1990ዎቹ የቢዝነስ ክስረት በገጠማቸው ጊዜ ሊያበድራቸው ፈቅዶ የነበረው አጋራቸው ዶቼ ባንክም ከዚህ የካፒቶል ሒል ክስተት በኋላ "ከእርስዎ ጋር ለመሥራት ይከብደኛል" በሚል ጥሏቸው ሄዷል።
ትራምፕ ከጎልፍ ሜዳዎችና ሆቴሎች እንዲሁም ሰማይ ጠቀስ የቢሮ ፎቆች በተጨማሪ በርከት ያሉ መለስተኛ አውሮፕላኖች አሏቸው። ከእነዚህ መካከል ቦይንግ 757 አውሮፕላኖች ይገኙበታል።
ብሉምበርግ እንደሚለው አብዛኞቹ የትራምፕ አውሮፕላኖች አሁን እያረጁ በመሆናቸው ገበያቸው ተቀዛቅዟል።
ከትራምፕ አውሮፕላኖች ውስጥ 7 የሚሆኑት በ2015 ግምታቸው 60 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን በ2020 ደግሞ 5 ሌሎች አውሮፕላኖች ግምታቸው 6 ሚሊዮን ብቻ ሆኗል። ይህም ከአውሮፕላኖቹ ዕድሜ ጋር የተያያዘ ነው።
ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ሁሉ ሀብት ውስጥ የፋይናንስ ሰነዶቻቸው ጥርጣሬን የሚጭሩ በመሆናቸው ለምርመራ ተጋልጠዋል።
ትራምፕ ምን ያህል ግብር እንደሚከፍሉ ለመግለጽ ሲተናነቃቸው ቆይቷል።
ባለፈው ወር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዶናልድ ትራምፕን የግብር ሰነዶቻቸውን ለዐቃቢ ሕግ ይፋ እንዲያደርጉ አዟቸዋል።
ይህ ምርመራ የተጀመረው በ2018 ቢሆነም እስከዛሬም አልተቋጨም።
ብዙ የሚዲያ መረጃዎች ትራምፕ የግብር ማጭበርበርና የግብር ስወራ እንደፈጸሙ የሚጠቁሙ ናቸው።
ትራምፕ ፕሬዝዳንት ሳሉ ያመለጣቸውን ትርፍ አሁን ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ከቲቪና ከመጽሐፍ ስምምነቶች በሚያገኙት ገንዘብ ያካክሱታል ተብሎ ይገመታል፡።
ባራክ ኦባማን ሚሼል ኦባማ ከአሳታሚዎች ጋር ባደረጉት ስምምነት በድምሩ 65 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሏቸዋል። ቢል ክሊንተን በ2014 ለሚጽፉት መጽሐፍ 15 ሚሊዮን ብር ቅድመ ክፍያ ተከፍሏቸው ነበር።
ትራምፕ የሚጽፉት መጽሐፍ አንባቢዎችን ይማርካል ተብሎ አይጠበቅም። የሰውየው ግንዛቤም ጥልቀት ይጎድለዋል ስለሚባል ትራምፕ ከመጽሐፍ የባራክ ኦባማን ያህል ትርፍ ያገኛሉ አይባልም።
ሆኖም 74 ሚሊዮን የሚገመቱ ተከታዮቻቸውን ሊማርክ የሚችል ትዕይነት በቴሌቪዥንና በማኅበራዊ የትስስር መድረክ በማቅረብ ዳጎስ ያለ ትርፍ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።












