የሴቶች ጥቃት፡ በአውስትራሊያ የሴቶችን ጥቃት በመቃወም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች አደባባይ ወጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውስትራሊያ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ወሲባዊ ጥቃቶችና ትንኮሳዎችን በመቃወም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች አደባባይ ወጡ።
ተቃዋሚዎቹ አደባባይ የወጡት በቅርቡ በአገሪቷ ምክር ቤት ላይ ያነጣጠሩ የወሲባዊ ትንኮሳ ክሶች ምክንያት ነው።
ክሶቹ በወግ አጥባቂው መንግሥት ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ተቃውሞው ለማካሄድ ዝግጅት የተጀመረው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክሪስቲያን ፖርተር እአአ በ1988 አስገድዶ መድፈር ፈፅመዋል መባሉ መሰማቱን ተከትሎ፤ ከአንድ ሳምንት በፊት ነበር።
እርሳቸው ድርጊቱን አልፈፀምኩም ብለው አስተባብለዋል።
በሌላም በኩል የቀድሞ ፖለቲካ አማካሪ ብሪታኒ ሂጊንስ የካቲት ወር ላይ እአአ በ2019 በሚኒስትሩ ቢሮ መደፈሯን መግለጿን ተከትሎ የሕዝብ ቁጣ ቀስቅሶ ነበር።
ተቃዋሚዎቹ መንግሥት ለወሲባዊ ጥቃት ክሶች የሚሰጠው ምላሽ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለዋል።
የቀድሞ ፖለቲካ አማካሪዋ ሂጊንስ ከምክር ቤቱ ደጅ ለተሰበሰቡት በሺዎች ለሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች "በአውስትራሊያ ሕብረተሰቡ የሴቶችን ጥቃት በሚያስፈራ ሁኔታ ችላ ብሎታል" ስትል ተናግራለች።
"ታሪኬን እንዲህ አደባባይ አውጥቼ የተናገርኩት ጥቃት በምክር ቤት የሚፈፀም ከሆነ በሌላ ቦታ የማይፈፀምበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ለማስታወስ ነው" ብላለች ሂጊንስ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'ማርች ፎር ጀስቲስ' በሚል የተዘጋጀው ተቃውሞው፤ ዋና ከተሞችን ካናቤራ፣ ሲድኒ እና ሜልበርንን ጨምሮ በአውስትራሊያ በሚገኙ 40 ከተማዎች ተካሂዷል።
አስተባባሪዎቹ አውስትራሊያ በታሪኳ ያየችው ከፍተኛው የሴቶች ድምፅ የተሰማበት የተቃውሞ ሰልፍ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ተቃዋሚዎቹ ጥቁር ልብስ ለብሰውና የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው ታይተዋል።
የካንቤራ ሰልፍ አስተባባሪዎች በምክር ቤቱ ላይ የሚቀርበውን ክስ በተመለከተ ከ90 ሺህ በላይ ፊርማዎች በማሰባሰብ ለሕግ አውጪዎች አቅርበዋል።
የመንግሥት ሚኒስትር ክርስቲያን ፖርተር ከኃላፊነታቸው እንዲነሱም ጥያቄ አቅርበዋል።
ምንም እንኳን ፖሊስ በዐቃቤ ሕጉ ላይ የቀረቡ ክሶችን ቢዘጋም፤ ሌሎች ግን በቀረበባቸው ክስ የተለየ ምርመራ እንዲደረግባቸው አሳስበዋል።
የመንግሥት ምላሽ ምን ነበር?
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰንን ተቃዋሚዎቹ ሊያገኟቸው አልፈቀዱም።
በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እሁድ ዕለት ስለ ጉዳዩ በምክር ቤት ለማነጋገር ተወካዮችን ጋብዘው ነበር። ነገር ግን የተቃውሞ አስተባባሪዎቹ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ምክንያታቸው ደግሞ እርሳቸው እና የመንግሥት የሴቶች ሚኒስትሮች ሰልፉ ላይ ያግኙን የሚል ነበር።
"ይኸው አሁን ደጃቸው ድረስ መጥተናል፤ አሁን ወደ እኛ መምጣት የመንግሥት ድርሻ ነው፤ በዝግ የምንነጋገርበት ጉዳይ አይኖርም" ብለዋል የሰልፉ አስተባባሪ ጃኒን ሄንድሪ በትዊተር ገጻቸው።
ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የመንግሥት ሕግ አውጪዎች ሰልፉ ላይ አልተገኙም።
ሆኖም የሌበር ተቃዋሚ ፓርቲ እና ሌሎች ታዋቂ ሕግ አውጪዎች በካንቤራ የተካሄደው ሰልፍን ተቀላቅለዋል።












