ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቢሊየነሯ የቀድሞ የጄፍ ቤዞስ ባለቤት የሳይንስ መምህር አገባች
ቢሊየነሯ ማኬንዚ ስኮት ልጆቿ በሚማሩበት ትምህርት ቤት ሳይንስ የሚያስተምር ግለሰብ አገባች።
ማኬንዚ ከዓለማችን ቁጥር አንድ ሃብታሙ ጄፍ ቤዞስ ጋር ፍቺ ከፈፀመች ሁለት ዓመት አልፏታል።
ማኬንዚ በዓለማችን ከሚገኙ ቁንጮ ሃብታም ሴቶች መካከል አንዷ ስትሆን እስካሁን ድረስ 4 ቢሊየን ዶላር ለእርዳታ ሰጥታለች።
ቢሊየነሯ የሳይንስ አስተማሪው ዳን ጄዌትን ማግባቷ ይፋ የሆነው 'ጊቪንግ ፕሌጅ' በተሰኘው የእርዳታ ድረ-ገፅ ላይ ነው።
"ዳን በጣም መልካም ሰው ነው፤ ሁለታችንም ደስተኛ ነኝ" ስትል ማኬንዚ ባወጣችው መግለጫ ስለ አዲሱ ትዳሯ ተናግራለች።
በፎርብስ መፅሔት የቅርብ ጊዜ ትንበያ መሠረት የማኬንዚ የተጣራ ሀብት 53 ቢሊየን ዶላር ገደማ ነው።
ቱጃሯ ማኬንዚ ከዚህ ሀብቷ ላይ ቆንጥራ ለእርዳታ ድርጅቶች ለመስጠት ቃል ገብታለች።
እርዳታ ለመስጠት ቃል ከገባችላቸው ድርጅቶች መካከል ሴቶች ላይ የሚሠሩ፣ የምግብ ባንኮችና የጥቁሮች ኮሌጆች ይገኙበታል።
ማኬንዚ ከጄፍ ቤዞስ ጋር ለ25 ዓመታት በትዳር የቆየች ሲሆን ቤዞስ በፈረንጆቹ 1994 ታዋቂውን ግዙፍ ድርጅት አማዞንን ሲያቋቁም ረድታዋለች።
ቱጃሯ ሁለት ልብ-ወለድ መፃሕፍትን አሳትማለች።
መፅሐፏ የሚሸጥበት የአማዞን ድር አምባ ላይ "ሲያትል ውስጥ ከአራት ልጆቿና ከባለቤቷ ዳን ጋር እንደምትኖር" ይገልፃል።
አዲሱ ባለቤቷ ዳን፤ የማኬንዚ ልጆች የሚማሩበት አንድ የሃብታም ትምህርት ቤት ውስጥ የሳይንስ አስተማሪ ነውም ይላል።
ቤዞስና ማኬንዚ በፈረንጆቹ 2019 ፍቺ ሲፈፅሙ ቤዞስ የዓለማችን የተረፈው ሃብታም ነበር።
የሀብቱ ዋነኛ ምንጭ ደግሞ በአማዞን ያለው 16 በመቶ ደርሻ ነበር። ማኬንዚ ፍቺው ሲፈፀም 4 በመቶውን ወስዳለች።
የአማዞኑ ጄፍ ቤዞስና የቴስላው ኢላን መስክ በየተራ የዓለማችን ቀዳሚ ሀብታሞች በመሆን እየተፎካከሩ ይገኛሉ።
ቢሊየነሯ ማኬንዚ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን 22ኛዋ ሀብታም ስትሆን የቀድሞ ባለቤቷ ደግሞ በ177 ቢሊየን ዶላር ቀዳሚውን ሥፍራ ይዟል።
'ጊቪንግ ፕሌጅ' የተሰኘው ድረ-ገፅ የተቋቋመው ከሀብታቸው ቆንጥረው ማበርከት ለሚፈልጉ ቢሊየነሮች ነው።
ድርጅቱ የተቋቋመው በቢልና ሜሊንዳ ጌትስ እንዲሁም በሌላኛው ባለጸጋ ዋረን ባፌት የዛሬ 11 ዓመት ገደማ ነበር።
ጄፍ ቤዞስ እስካሁን ድርጅቱን አልተቀላቀለም።