ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መስፈርት ሳያሟሉ የኮቪድ-19 ምርመራ ለሚያደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጠ
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተገቢውን መስፈርት ሳያሟሉ የኮቪድ-19 ምርመራ የሚያደርጉ ተቋማት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ ሰጠ።
ኢንስቲትዩቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ተገቢውን መስፈርት ሳያሟሉ የኮቪድ-19 ምርመራ የሚያደርጉ ተቋማት መኖራቸውን ደርሼበታለሁ ብሏል።
“በቅርቡ ‘የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራ እናደርጋለን እስከ 6 ሰዓትም ውጤት እናሳውቃለን’ እያሉ ማስታወቂያ የሚያሰራጩ ተቋማት መኖራቸውን ደርሰንበታል” ብሏል የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ ባወጣው መግለጫ።
ኢንስቲትዩቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሶ፤ የላብራቶሪ ማስፋፊያ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በምርምር ተቋማት፣ በክልል ላብራቶሪዎች፣ በዩኒቪርቲዎች እንዲሁም ከግል ተቋማት ጋር በመተባበር የኮቪድ-19 ምርመራ ተቋማት ተስፋፍተዋል ብሏል።
ኢንስቲቲዩቱ እስካሁን ተገቢውን መስፈርት ያሟሉ የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራ ፍቃድ የተሰጣቸው የግል ተቋማት ብዛት 15 ናቸው ያለ ሲሆን የተቋማቱን ዝርዝር በፌስቡክ ገጹ ላይ አውጥቷል።
ኢትዮጵያ እስካሁን ከ2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርምራ አድርጋ 158ሺህ 053 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጣለች።
ከጤና ሚንስቴር በሚሰጠው ዕለታዊ የኮቪድ-19 ወቅት መግለጫ መሠረት ቫይረሱ በኢትዮጵያ ሪፖርት ከተደረገ ወዲህ 134ሺህ 736 ሰዎች ከበሽታው ሲያገግሙ፤ 2ሺህ 354 ሰዎች ከበሽታው ጋር በተያያዙ ሕመሞች ህይወታቸው አልፏል።