ሰባት የኒጀር የምርጫ ኮሚሽን አባላት በፈንጅ ፍንዳታ ሕይወታቸው አለፈ

ታትሟል

በኒጀር ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ድምጽ መስጫ ዕለት ሰባት የምርጫ ኮሚሽን አባላት በፈንጅ ፍንዳታ ሕይወታቸው አለፈ።

የአገሪቱን የምርጫ ኮሚሽን አባላት የያዘው መኪና በአገሪቱ ደቡብ ምዕራብ በሚገኘው ቲላቤሪ ክልል ፈንጂ ላይ ሄዶ ነው አደጋው የደረሰው።

ተሽከርካሪው ሆን ተብሎ ዒላማ ስለመደረጉ ግን የታወቀ ነገር የለም። በፍንዳታው ከተገደሉት 7 ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ሠራተኞች ቆስለዋል።

ኒጀር በጎርጎሮሳዊያኑ 1960 ከፈረንሳይ ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ ለሁለተኛው ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ህዝቡ ትናንት ድምጽ ሲሰጥ ውሏል።

“[ሠራተኞቹ] የምርጫ ሳጥኖቹን እና የምርጫ ጣቢያ ሰራተኞችን እያደረሱ ነበር” ሲሉ የአከባቢው የምርጫ ኮሚሽን ኃላፊ ሀሩና ሞንካይላ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

በዚህ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የገዢው ፓርቲ ተወካይ የቀድሞው የአገር ውስጥና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሃመድ ባዙም በመጀመሪያው ዙር 40 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል ተብሏል።

ለማሸነፍ ቅድሚያ ግምት የተሰጣቸው ዕጩ ተወዳዳሪም ናቸው።

ተቀናቃኛቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ማሃመኔ ኦስማን ሲሆኑ በመጀመሪያው ዙር 17 በመቶ ድምጽ ያገኙ ሲሆን የበርካታ አነስተኛ ፓርቲዎች ድጋፍ አላቸው።

ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት መሃማዱ ኢሱፉ ከሁለት የአምስት ዓመት የሥልጣን ጊዜ በኋላ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ተዘጋጅተዋል።

ኒጀር በዓለም ላይ ካሉ በጣም ድሃ አገራት አንዷ ስትሆን በሳህል የሚንቀሳቀሱ እስላማዊ ታጣቂዎች የፀጥታ ስጋት ጋርጠውባታል።