የካናዳ ፓርላማ በቻይና የአናሳ ማኅበረሰቦች አያያዝ አሳሳቢነት ላይ ውሳኔ አሳለፈ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የካናዳ ምክር ቤት ቻይና በአገሪቱ ያሉ አናሳ ቁጥር ያላቸው የዊጉርስ ሕዝቦች የያዘችበት መንገድ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ሲል በአብላጫ ድምፅ ድምጽ ወሰነ።
ካለተቃውሞ በ266 በሆነ ድምጽ በተላለፈው ውሳኔ በሁሉም የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በገዢው ሊበራል ፓርቲ የሕግ አውጭዎችም ድጋፍ አግኝቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ እና አብዛኛዎቹ የካቢኔ አባላቶቻቸው ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል።
ካናዳ ውሳኔውን በማጽደቅ ከአሜሪካ በመቀጠል ቻይና የፈጸመችውን የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደሆነ እውቅና የሰጠች ሁለተኛዋ አገር እንድትሆን አድርጓታል።
የሕግ አውጭዎቹ በተጨማሪም "የቻይና መንግሥት እልቂቱን ካስቀጠለ" ካናዳ ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በጎርጎሮሳዊያኑ 2022 የክረምት ኦሊምፒክን ቤጂንግ እንዳታዘጋጅ ጥሪ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ትሩዶ እስካሁን ድረስ ቻይና በዢንጂያንግ አናሳ ቁጥር ባላቸው የዊጉርስ ተወላጆች ላይ የወሰደችውን እርምጃ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው በማለት ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት ተጨማሪ ምርመራ ያስፈልጋል ብለዋል።
ከካቢኔ አባላቶቻቸው መካከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርክ ጋርኑ ብቻ ድምፅ ለመስጠት በፓርላማ ተገኝተዋል። ጋርኑ በጋራ ምክር ቤት ተገኝተው ሲናገሩ "በካናዳ መንግሥት ስም" ድምፀ ተአቅቦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ኤሪን ኦቶሌ ከድምጽ አሰጣጡ ቀደም ብለው ውሳኔው "አንዳንድ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን መስዋዕት ማድረግ ቢጠበቅብንም ለሰብአዊ መብቶች እና ለሰብአዊ መብቶች ክብር እንደምንቆም ግልጽና የማያሻማ መልዕከት ለመላክ አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
ኦቶሌ በዚህ ወር መጀመሪያ ለጠቅላይ ሚንስተሩ "ቻይና ጋር እንድትቆም" ለመጠየቅ በሚል በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ቢቢሲ በቻይናዋ ዢንጂያንግ "የተሃድሶ ትምህርት" ካምፖች ውስጥ ስልታዊ አስገድዶ መድፈር፣ ወሲባዊ ጥቃት እና ማሰቃየት መከሰቱን መዘገቡን ተከትሎ ቢቢሲ ወርልድ ኒውስን ማገዷን እንደማሳያ አንስተዋል።
የሰኞ ዕለቱ አስገዳጅ ያልሆነው ውሳኔ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተበላሸ በሄደው የካናዳ እና የቻይና ግንኙነት መባባሱን ያሳያል።
በሳምንቱ መጨረሻ በካናዳ የቻይና አምባሳደር የሆኑት ኮንግ ፒዩው ለካናዳ ፕሬስ እንደተናገሩት እንቅስቃሴውን "ጣልቃ ገብነት" ነው ብለውታል።
"ከእውነታው ጋር ስለሚጋጭ በጥብቅ እንቃወማለን። በዢንጂያንግ በጭራሽ ምንም የዘር ማጥፋት ወንጀል የለም" ብለዋል።
የመብት ተሟጋቾች ቡድኖች ቻይና ባለፉት ጥቂት ዓመታት "የተሃድሶ ትምህርት ካምፖች" ብሎ በገለጸው እንቅስቃሴው እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ዊጉርሶችን እንደሰረች ያምናሉ።
የቢቢሲ ያደረጋቸው ምርመራወዎች እንደሚያመለክቱትም ዊጉርሶችን በአስገዳጅ የጉልበት ሥራ እየተጠቀሙባቸው ነው።
የካናዳ አስገዳጅ ያልሆነ ውሳኔ ቀጣይ እርምጃዎችን ባያስቀምጥም መንግሥታቸው የአሜሪካን አካሄድ መከተል አለበት ይላል።
የወቅቱ እና የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቻይና በምዕራብ ዢንጂያንግ ግዛት በሚገኙ በዊጉር ሙስሊሞች እና በሌሎች አናሳ ሕዝቦች ላይ ያነጣጠረው ፖሊሲዋ የዘር ማጥፋት ወንጀል መሆኑን አስታወቀዋል።















