የአርሰናሉ ሜሱት ኦዚል ስለ ቻይና ሙስሊሞች የሰጠው አስተያየት ክርክር አስነሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአርሰናሉ መሀል ክፍል ተጫዋች ሜሱት ኦዚል በቻይና ስለሚገኙ ኡጉር ሙስሊሞች የሰጠው አስተያየት የሰጠው አስተያየት መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ ቡድኑ አርሰናል ጉዳዩ እኔን አይመለከተኝም የሚል መግለጫ እስከማስወጣት ደርሷል።
ቻይና በሚሊየን የሚቆጠሩ የኡጉር ሙስሊም ማህበረሰቦችን ያለፍርድቤት ትእዛዝ አስራለች፤ በማጎሪያ ካምፖችም ታሳቃያቸዋለች በማለት አንዳንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ይከሳሉ።
ቻይና በበኩሏ ማዕከላቱ ሀይማኖታዊ አክራሪነትን ለመዋጋት የሚረዱ የቴክኒክና ስልጠና ማስተማሪያዎች እንጂ ማጎሪያ ካምፖች አይደሉም በማለት በተደጋጋሚ ገልጻለች።
ሜሱት ኦዚል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈረው መልእክት የኡጉር ሙስሊሞችን ''እስራትና ስቃይን መቋቋም የሚችሉ ተዋጊዎች'' ብሎ በማድነቅ፤ ቻይና እና ዝምታን መርጠዋል ያላቸው ሌሎች ሙስሊሞችን ተችቷል።
የአርሰናል እግር ኳስ ክለብ በበኩሉ ''አርሰናል እንደ ድርጅት ከፖለቲካ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም'' ብሏል።
አክሎም '' ሜሱት ኦዚል በማህበራዊ ሚዲያ ያስተላለፈውን መልእክት ተከትሎ የአርሰናል እግር ኳስ ክለብ ጉዳዩ እንደማይመለከተውና የኦዚል የግል ሃሳብ መሆኑን መግለጽ እንፈልጋለን'' ብሏል።
የመድፈኞቹ መግለጫ በቻይናው ማህበራዊ ሚዲያ ዌቦ ላይ ነው የተላለፈው።
የኦዚልን አስተያየት ተክትሎ በርካታ የአርሰናል ደጋፊዎች ቡድኑ ጉዳዩን በጥልቀት እንዲከታተለውና ከመግለጫ ያለፈ እርምጃ እንዲወስድ አስተያየታቸውን ገልጸዋል።
ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ ኦዚል ተገቢ ያልሆነ አስተያየት ስለ ቻይና ሰጥቷል፤ ሊቀጣም ይገባል ያሉ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ኦዚልን ማሊያ ቀደው ምስሉን ሲያጋሩ ነበር።
የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ ቡድን ባለፈው ዓመት ይፋ ባደረገው ልዩ ጥንቅር ቻይና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊም ዜጎችን የምታጉርበት የበረሃ ካምፕ መኖሩን አጋልጧል።
"የዕደ ጥበብ ማሰልጠኛ" በሚል ሽፋን ለዓመታት የቆየው ይህ ካምፕ አስተሳሰብን የሚያጥብ፣ ጉልበትን የሚያዝል፣ እምነትን የሚሸረሽር፣ ኅቡዕ የግዞት ማዕከል ነበር ተብሏል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ በማዕከሉ ገብተው የሚወጡ ዜጎች ሃይማኖታቸውን ብቻ ሳይሆን ጨርቃቸውን ሊጥሉ ይችላሉ።
ቻይና በበኩሏ "የአክራሪ ሙስሊሞች ሞገደኛ አስተሳሰብ የምገራበት ከፍተኛ የትምህርትና ሥልጠና ተቋሜ ነው" ትላለች።












