የአሜሪካዊያን አማካይ የዕድሜ ጣሪያ በአንድ ዓመት አሽቆለቆለ

በካሊፎርኒያ የምትገኝ ነርስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አሜሪካዊያን በዚህች ምድር ላይ በአማካይ የሚኖሩበት ዓመት በተገባደደው የፈረንጆቹ ዘመን [2020] በአንድ ቀንሷል።

ለዚህ የአማካይ ዕድሜ ጣሪያ መቀነስ ዋነኛው ምክንያት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ነው ተብሏል።

የአሜሪካዊያን አማካይ ዕድሜ ወደ 77.8 በመቶ መውረዱን ያሳወቀው የበሽታ ቁጥጥር ማዕከል ነው።

"ይህ ከበድ ያለ ማሽቆልቆል ነው" ብለዋል የማዕከሉ የሞት መረጃ ኃላፊ ዶ/ር ሮበርት አንደርሰን።

ከዚህም አልፎ የተለያየ የዘር ግንድ ያላቸው አሜሪካዊያን አማካይ ዕድሜ ጣሪያ የበለጠ ማሽቆልቆሉን ኃላፊው ይናገራሉ።

ለምሳሌ የጥቁር አሜሪካዊያን ወንዶች የዕድሜ ጣሪያ ከጥር እስከ ሰኔ [2020] ባለው ጊዜ በሶስት ዓመት መቀነሱ ታውቋል።

በሌላ በኩል የሂስፓኒክ ዘር ያላቸው ወንዶች ጣሪያ በ2.4 ዓመት ቀንሷል።

"እንዲህ ዓይነት የዕድሜ ጣሪያ ማሽቆልቆል የታየው በ1940ዎቹ በነበረው የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ነው" ይላሉ ዶ/ር አንደርሰን።

የአሜሪካዊያን ዕድሜ ጣሪያ በአንድ ዓመት ቀነሰ ማለት አሜሪካዊያን ወንዶች የዕድሜ ዘመናቸው በአማካይ 75.1 ሆነ ማለት ነው።

ይህ ቁጥር ከ2019 [በፈረንጆቹ] ጋር ሲነፃፀር በ1.2 ዓመት ያሽቆለቆለ ነው።

በተያያዘ የአሜሪካዊያን ሴቶች የዕድሜ ጣሪያ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ በመቀነስ ወደ 80.5 አሽቆልቁሏል።

የማዕከሉ ዘገባ እንደሚጠቁመው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ የተከሰተው ሞት ለዕድሜ ጣሪያ መቀነስ ዋነኛ ምክንያት ነው።

አሜሪካ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ከ490 ሺህ በላይ ዜጎቿን አጥታለች። ይህ ቁጥር በኮቪድ-19 ሞት ከዓለም አንደኛ ያደርጋታል።

ከማዕከሉ የተገኙ መረጃዎች በተዘዋዋሪ የሚያመለክቱት ወረርሽኙ አሜሪካ ውስጥ ያሉ ነጭ ያልሆኑ ሰዎችን ምን ያህል እየጎዳ እንደሆነ ነው።

ጥቁር አሜሪካዊያን ከነጭ አሜሪካዊያን በሶስት እጥፍ በኮሮናቫይረስ የመሞት ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው።

ብሩኪንግስ የተባለ ተቋም ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ባወጣው ጥናት በእያንዳንዱ የዕድሜ ክፍል ጥቁር አሜሪካዊያን ከነጭ አሜሪካዊያን በላቀ በኮቪድ እየሞቱ እንደሆነ አመላክቶ ነበር።

የአሜሪካ በሽታ ቁጥጥር ማዕከል ጥናቱን የሰራው በስድስት ወራት ከሰበሰባቸው ቁጥሮች ተነስቶ እንደሆነ ይናገራል።

ይህ ማለት የጥናቱ ውጤት የወረርሽኙን ሙሉ ምስል ላያሳይ ይችላል ማለት ነው ይላል ማዕከሉ።

ሌላው ደግሞ በሽታው የተለያዩ አካባቢዎችን በተለያዩ ጊዜያት ማጥቃቱ ምናልባት ወደፊት የተለየ ውጤት ሊመጣ እንደሚችል ማሳያ ነው።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመጀመሪያዎቹ ወራት ያጠቃው በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ነው።

ከኮሮናቫይስ ወረርሽኝ በተጨማሪ በ2020 በሐኪም የሚታዘዙ መድኃኒቶችን ያለልክ መውሰድ ሌላኛው የሞት ምክንያት ሆኖ ተመዝገቧል።

የአሜሪካዊያን አማካይ የዕድሜ ጣሪያ በፈረንጆቹ 2014፥ 78.9 ደርሶ ነበር። ይህም በታሪክ ትልቁ ነው።