አሜሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ሜክሲኮ የሚገኙ ስደተኞችን ልትቀበል ነው

አሜሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ሜክሲኮ የሚገኙ ስደተኞችን ልትቀበል ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

የጆ ባይደን አስተዳደር ሜክሲኮ የሚገኙ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ አሜሪካ እንዲገቡ እንደሚፈቅድ አስታወቀ።

ስደተኞቹ ወደ አሜሪካ መግባት ስላልቻሉ ሜክሲኮ ሆነው ለመጠባበቅ ተገድደው ነበር። በቀጣዩ ሳምንት 25,000 ስደተኞች ወደ አሜሪካ ይገባሉ።

በሦስት የድንበር ኬላዎች እንዲገቡ የሚፈቅዳለቸው ስደተኞች መጀመሪያ ላይ የኮቪድ-19 ምርመራ ያደርጋሉ።

የቀድሞው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞችን በሚያገል ፓሊሲያቸው ይተቻሉ።

እአአ በ2019 የወጣው የስደተኞች ፓሊሲ ጥገኝነት ጠያቂያዎች ጉዳያቸው በአሜሪካ እስኪታይ ሜክሲኮ እንዲቆዩ ያስገድዳል። ባይደን በመጀመሪያው የሥልጣን ቀናቸው ይህንን ፖሊሲ ሰርዘዋል።

ሰብዓዊ፣ ደንብ የተከተለ እና ደህንነቱ የሚያስተማምን የስደተኞች ሥርዓት ባይደን እንደሚዘረጉም ተነግሯል።

የባይደን አስተዳደር በሜክሲኮ ድንበር ሁለት ኬላዎች በቀን 300 ስደተኞችን ከመቀበል ይጀምራል። ስደተኞቹ ጉዳያቸውን ለፍርድ ቤት የሚያቀርቡበት ቀን ይሰጣቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚኖሩበት ቦታ ይመቻቻል።

ይህ ውሳኔ በሜክሲኮ የስደተኞች ማቆያ ሆነው ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚጠባበቁ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እጅግ አስደስቷል።

አንድ የሳልቫዶር ተወላጅ "የተሰማኝን ደስታ ለመግለጽ በቂ ቃላት የለኝም" ስትል ለሮይተርስ ተናግራለች።

ስደተኞች ወደ አሜሪካ ለመግባት በሚጠባበቁባቸው አካባቢዎች ወንጀል በመስፋፋቱ አደገኛ ሆኗል።

ሂውማን ራይትስ ፈርስት የተባለ የተራድኦ ድርጅት አምና ባወጣው መግለጫ ቤተሰቦችና ታዳጊዎች አፈና፣ ወሲባዊ ጥቃትና ሌሎችም እንግልቶች ይደርሱባቸዋል ብሏል።