ናይጄሪያውያን ሼልን በዩኬ ፍርድ ቤት መክሰስ ይችላሉ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, LEIGH DAY
በሼል ምክንያት አካባቢያቸው የተበከለባቸው ናይጄሪያውያን ድርጅቱን በዩናይትድ ኪንግደም ፍርድ ቤት መክሰስ እንደሚችሉ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወሰነ።
ላለፉት አምስት ዓመታት ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ ለነበሩ የኒጀር ዴልታ ነዋሪዎች ይህ ውሳኔ ትልቅ ድል ነው።
በኒጀር ዴልታ ከ 40,000 በላይ ሰዎች ይኖራሉ። ሼል ባስከተለው የአካባቢ ብክለት የተነሳ ጤናቸው እንደተቃወሰና ሕይወታቸው ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸውም ይናገራሉ።
ሼል በበኩሉ በናይጄሪያ ሕግ መዳኘት ያለበት ሌላ ድርጅት ወኪል እንደሆነ ይከራከራል።
የዩኬ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን ቢል እና ኦጋል በሚባሉት ማኅበረሰቦች ሮያል ደች ሼል ላይ የቀረበው ክስ በዩኬ ፍርድ ቤት መዳኘት ይችላል ሲል ውሳኔ አስተላልፏል።
ሮያል ደች ሼል የአየር ብክለት እንደተከሰተ ባይክድም በናይጄሪያ ቅርንጫፉ ጉዳይ ተጠያቂ መሆን እንደሌለበት ተከራክሯል።
ባለፈው ዓመት አቤቱታ ሰሚ ፍርድ ቤት የሼልን ቅሬታ ቢቀበልም፤ ዘንድሮ ግን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሽሯል።
ሼል በዴልታ ካለው የነዳጅ ምርት 50% ይሸፍናል።
ክስ ለመሠረቱት ሰዎች ጥብቅና የቆመው ሊግ ደይ፤ ሼል ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ኃላፊነት የመውሰድ ግድታ እንዳለበት ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል። ድርጅቱ የአካባቢ ጥበቃና የሰዎች ደህንነት ጉዳይን ችላ እንዳለም ተጠቁሟል።
ጠበቃ ዳንኤል ላደር "ጉዳት የደረሰባቸው ማኅበረሰቦች ሀያል ተቋሞች ግዴታቸውን እንዲወጡ ማድረግ እንደሚችሉ ማሳያ ነው" ብሏል።
ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች አምነስቲም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አሞግሷል።
"ይህ ውሳኔ ሼል እና ሌሎችም ሰብዓዊ መብት የሚጥሱ ድርጅቶች ተጠያቂ እንዲሆኑ ያስችላል።" ሲሉ የድርጅቱ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ፕሮግራም ኃላፊ ተናግረዋል።
ሼል ግን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ "አሳዝን ነው" ብሏል።












