ሽጉጥ ይዘው የገቡት እንደራሴ በኬንያ ፓርላማ ድንጋጤን ፈጠሩ

የኬንያ ፓርላመንት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በትናንትናው ዕለት የኬንያ ፓርላማ አባል የሆኑት ግለሰብ ሽጉጥ ታጥቀው መምጣታቸውን ተከትሎ በምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ከፍተኛ ፍራቻ ተፈጥሮ እንደነበር ተገልጿል።

ኤላይሻ ኦድሂያምቦ የተባሉት እንደራሴ ለምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ፣ አቻቸው በኮታቸው ውስጥ ሽጉጥ ሻጥ እንዳደረጉ ማየታቸውን ተናገሩ።

ሽጉጥ ይዘዋል የተባሉት ሌላኛው እንደራሴ መሃመድ አሊ ይባላሉ።

አፈ ጉባኤው ጀስቲን ሙቱሪ በበኩላቸው መሃመድ አሊን ሽጉጥ ይዘው እንደሆነ ጠየቋቸው።

"በጣም ይቅርታ፤ ዕቃዬን ውጭ ሳላስቀምጥ ገባሁ። ያው ከሰው ስህተት አይጠፋም" በማለት ቢናገሩም አፈ ጉባኤውም ደግመው ሽጉጥ ይዘው እንደሆነ ይናገሩ አሏቸው።

"እባክዎ አፈ ጉባኤ ሽጉጡን እንዳስረክብ ጊዜ ይሰጠኝ" ሲሉም ከምክር ቤቱ ካሜራ ውጭ ለመሆን እየሞከሩ ተናግረዋል።

ህጉ በሚያዘው መሰረት ውጭ ለሚገኘው የፓርላመንቱ የጥበቃ ኃላፊ እንዲያስረክቡ ተደርገዋል።

አፈ ጉባኤው ለጥበቃ ኃላፊው ሁኔታውን በትኩረት እንዲከታተል ትዕዛዝ ከመስጠት በተጨማሪ "አስደንጋጭ እይታ ነው" ብለውታል።

መሐመድ አሊ በበኩላቸው አቻ እንደራሴዎች ነገሩን ይፋ በማድረጋቸው ብስጭታቸውን ከመግለፅ በተጨማሪ የተደበቀ ፖለቲካዊ አንድምታ አለው ብለዋል።

የጠቆሟቸው እንደራሴና መሃመድ አሊ የተለያዩ ፓርቲ አባላት ናቸው።

ሚሊ ኦድሂያምቦ የተባሉ ሌላ እንደራሴ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ በከፍተኛ ከመጋጋሉ ጋር ተያይዞ ጥብቅ የሆነ የደህንነት ጥበቃ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኬንያ የህግ መምሪያ ምክር ቤት አባላት በአገሪቱ ውስጥ መሻሻል አለበት ስለሚባለው ህገ መንግሥት ጉዳይ ተከፋፍለው ይገኛሉ።

የአገሪቱ ፕሬዚዳንትና ምክትላቸው ህገ መንግሥት ማሻሻያውን አስመልክቶ የሚደረገው ህዝበ ውሳኔ ላይ የተለያየ ምልከታ አላቸው።