ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባይደን የትራምፕ የድንበር ግንብ ፕሮጀክት ገንዘብ እንዲቋረጥ አደረጉ
ከሜክሲኮ የሚመጡ ስደተኞችን እንዳይገቡ ለማድረግ ትራምፕ ይዘውት የነበረውን የድንበር ግንብ ፕሮጀክት ገንዘብ፣ አዲሱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እንዲቋረጥ አደረጉ።
ፕሬዚዳንቱ ለምክር ቤቱ በላኩት ደብዳቤ የማይሻር ያሉትን ውሳኔ እንዳስተላለፉና ግብር የሚከፍለው ማህበረሰብ ገንዘብ ይህንን ግንብ ለመገንባት አይውልም ብለዋል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን በሚያዋስናት ድንበር በኩል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካሳለፉ በኋላ ለጦሩ የተያዘውን በጀት ወደ ድንበሩ ግንብ ግንባታ እንዲውል አድርገው ነበር።
ትራምፕ ከስልጣን ሲሰናበቱም ለፕሮጀክቱ 25 ቢሊዮን ዶላር ፈጅተዋል ተብሏል።
የትራምፕን ፖሊሲዎችና አጀንዳዎች መቀልበስና ማስተካከል ዋነኛ አጀንዳ አድርገው የያዙት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ይህ ቁልፍ ውሳኔያቸውም ከዚያ ጋር የተያያዘ ነው።
በባለፈው ሳምንት እንዲሁ የትራምፕን ፖሊሲ ተከትሎ ተለያይተው የነበሩ ስደተኛ ቤተሰቦች እንዲገናኙ የሚያደርግ ውሳኔን አስተላልፈዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የትራምፕ የስደተኞች ፖሊሲ ላይ ምርመራ እንዲከፈት አዘዋል።
ሃሙስ እለት ፃፉት በተባለው ደብዳቤ ለግድቡ ግንባታ ዋለ የተባለው ገንዘብ ላይ ኦዲት እንደሚደረግ ጠቅሰው አስፍረዋል።
ለትራምፕ የ2016ቱ ምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ዋነኛ አጀንዳቸው የነበረው የድንበሩ ግንብ ግንባታ ነበር።
ሆኖም ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከዲሞክራቶች በኩል ባጋጠማቸው ተቃውሞ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውሳኔን በመጠቀም የምክር ቤቱን ስልጣን ተላልፈው ግንቡን መገንባት ጀምረው ነበር።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፕሬዚዳንቶች ያለውን የስልጣን እርከን እንዲያልፉና የጦሩ በጀትንም አስፈላጊ ነው ለሚሏቸው ፕሮጀክቶች እንዲያውሉ ይረዳቸዋል።
ትራምፕ ስልጣን ከመቆጣጠራቸው በፊትም ድንበሩ ላይ 1 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን አጥር ነበር።
በስልጣናቸው ወቅትም ተጨማሪ ኪሎሜትሮችን እንዲሁም የነበረውን ግንብ ከፍ በማድረግና በማጠናከር ስራ ተጠምደው ነበር።