ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩስያ አዲስ ማዕቀብ ከተጣለብኝ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋርጣለሁ አለች
ሩስያ ምጣኔ ሀብቷን የሚያዳክም አዲስ ማዕቀብ የሚጣልባት ከሆነ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላትን ግንኙነት እንደምታቋርጥ አስታወቀች።
በእስር ላይ የሚገኘው ተቃዋሚው አሌክሲ ናቫልኒ የተያዘበትን ሁኔታ በተመለከተ የአውሮፓ ሕብረት ቅሬታ አሰምቷል። ተጨማሪ ማዕቀቦች ሩስያ ላይ ለመጣልም ዝቷል።
ሩስያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላትን ግንኙነት ልታቋርጥ እንደሆነ የተጠየቁት የሩስያው የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ "ግንኙነታችንን ለማቋረጥ ዝግጁ ነን። ሰላም የምትፈልጉ ከሆነ ለጦርነት ዝግጁ መሆን አለባችሁ" ብለዋል።
ተጨማሪ ማዕቀቦች የሚጣሉ ከሆነ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደሚያቋርጡም ተናግረዋል።
ሚንስትሩ ከሩስያ ዩቲዩብ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "ማዕቀቦች ምጣኔ ሀብታችንን ይጎዳሉ። ከዓለም ጉዳዮች ራሳችንን ማግለል ባንፈልግም ዝግጁ መሆን አለብን" ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት ሩስያ እና የአውሮፓ ሕብረት አንዳቸው የሌላቸውን ዲፕሎማቶች አስወጥተዋል። ይህም ከናቫልኒ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ነው።
መጀሪያ የአውሮፓ ሕብረት ዲፕሎማትን ያስወጣችው ሩስያ ናት። ዲፕሎማቶቹ በሕገ ወጥና ናቫልኒን በሚደግፍ የተቃውሞ ሰልፍ ተሳትፈዋል ብላ ነው ከአገሯ ያባረረችው።
የአውሮፓ ሕብረት የሩስያን ክስ አጣጥሏል።
በዚህ ሳምንት ጀርመን፣ ፖላንድ እና ስዊድን ሦስት የሩስያ ዲፕሎማቶችን አባረዋል።
ባለፈው ጥቅምት የአውሮፓ ሕብረት በስድስት ከፍተኛ የሩስያ ባለሥልጣኖች ላይ ማዕቀብ መጣሉ አይዘነጋም።
ከናቫልኒ መመረዝ ጋር ቀጥታ ግንኙነት አለው የተባለ የሩስያ የኬሚካል መሣሪያ ማዕከል ላይም ማዕቀብ ተጥሏል።
ነሐሴ ላይ ናቫልኒ ተመርዞ ለሞት ተቃርቦ ነበር። ጀርመን ሕክምና ተከታትሎ ወደ ሩስያ ከተመለሰ በኋላ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ብዙ የፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቅርብ አጋሮች በአውሮፓ ሕብረት እና አሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል። ገንዘባቸው ታግዷል። እንዳይጓጓዙም ተከልክለዋል።
ሩስያ ላይ ማዕቀቦች መጣል የጀመሩት በተለይም እአአ በ2014 ዩክሬንን በግድ የግዛቷ አካል ካደረገች ወዲህ ነው።
የአውሮፓ ሕብረት የካቲት 22 በሩስያ ጉዳይ ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።