ክራባት ባለማሰራቸው የተባረሩት የፓርላማ አባል እንዲመለሱ ተደረገ

ታትሟል

በኒውዚላንድ የማኦሪ ማህበረሰብን ወክለው የፓርላማ አባል የሆኑት ግለሰብ ክራባት አላስርም ማለታቸውን ተከትሎ በፓርላማው ውዝግብ አስነስቷል።

ራዊሪ ዋይቲቲ የተባሉት ግለሰብ በክራባት ፈንታ ሄይ ቲኪ የተባለውን ባህላዊውን የማኦሪ ጌጥ በማድረጋቸው የአለባበሱን ስርዓት ጥሰዋል ተብለው ከፓርላማ እንዲወጡ ተደርገው ነበር።

ከአንድ ቀን በኋላ ግን ፓርላማው እንዲመለሱና በባህላዊው ጌጣቸው ምክር ቤቱ ውስጥ እንዲናገሩ ፈቅዶላቸዋል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ በፓርላማው ክራባት ማሰር አስገዳጅነቱ እንደቀረ ተናግረዋል።

ሪዊሪ ዋይቲቲ ይህንን ውሳኔ በፀጋ የተቀበሉት ሲሆን "ለመጪው ትውልድ ከፍተኛ ማሸነፍ ነው" ብለውታል።

በዚህም መሰረት ምክር ቤቱ ሰዎች በፈለጉበት መንገድ ባህላዊ ማንነታቸውን በነፃነት የሚገልፁበት ስፍራ ያደርገዋል በማለት ሊቢሲው ኒውስ ደይ ፕሮግራም ተናግረዋል።

አክለውም "የማኦሪ ማህበረሰብ ከ181 ዓመታት በላይ በራሱ ባህል እንዲያፍርና እንዲዋጥ ያደረገው ጭቆና አካል ነው" ብለውታል።

በኒውዚላንድ የምክር ቤት የአለባበስ ህግ መሰረት ወንዶች የፓርላማው አባላት ጥያቄ መጠየቅ የሚችሉት ክራባት ሲያስሩ ብቻ ነው። ይህንንም ጥሰዋል ተብለው በትናንትናው ዕለት ከፓርላማው እንዲወጡ ተደርገው ነበር።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ትሬቨር ማላርድ የማኦሪ ፓርቲ መሪ የሆኑትን ሪዊሪን እንዳይናገሩ ሁለት ጊዜ ከከለከሏቸው በኋላ ከፓርላማው እንዲወጡ ተደርገዋል።

"ይሄ የክራባት ጉዳይ አይደለም፤ የባህላዊ ማንነት እንጂ ወዳጄ" በማለትም ተናግረው ምክር ቤቱን ለቀው ወጥተው ነበር።

የክራባቱ ጥያቄ ከዚህ ቀደምም የተነሳባቸው ሪዊሪ ባለፈው አመትም እንዲሁ ክራባት ካላሰሩ ከምክር ቤቱ እንደሚወጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር።

የፓርላማ አባሉ በበኩላቸው "የቅኝ ግዛት ማነቆ" ሲሉ ጠርተውታል።

በዛሬው ዕለት ወደ ፓርላማ ከተመለሱ በኋላ የባህላዊውን የማኦሪ ጌጥ በማድረግ ጥያቄያቸውን ጠይቀዋል።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርንደን ከዚህ ቀደም ክራባት ማድረግ የማይፈልጉ የፓርላማ አባላት እንዳሻቸው እንዲሆኑና ከዚህ በላይ አገሪቷን የሚያስጨንቃትና ልንሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ ብለው ነበር።

"ኒውዚላንዳውያን ክራባት ማሰር የሚያስጨንቃቸው ጉዳይ አይመስለኝም" ብለዋል።