ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለሊቢያ ሰላምን ያመጣል የተባለ ድምጽ ተሰጠ
የተለያዩ ቡድኖችን ወክለው የተገኙ አካላት በጄኔቭ በተባበሩት መንግሥታት በሚመራ ፎረም ላይ ለአምስት ቀን ውይይት ካደረጉ በኋላ ሶስት አባላት ያሉት የፕሬዝደንት እና ጠቅላይ ሚንሰትር መማክርት ለመመስረት ከስምምነት ደረሱ።
ይህ ስምምነት ባለፈው ዓመት ከተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ጋር ተዳምሮ ለአገሪቷ ሰላም መልካም ዜና ነው ተብሏል።
እአአ 2011 ላይ ሊቢያን ለበርካታ ዓመታት የመሩት ሙአመር ጋዳፊ በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) መራሹ ኃይል ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ሊቢያ ቀውስ ውስጥ ሆና ቆይታለች።
በአህጉሪቱ ግዙፍ የነዳጅ ክምችት ያላት ሊቢያ በተለያዩ ፍላጎት በተደራጁ በርካታ ሚሊሻዎች ስትታመስ ቆይታለች። መዳረሻቸውን አውሮፓ ለማድረግ ለሚሹ ስደተኞችም ቁልፍ የመሸጋገሪያ ስፍራ ሆና ቆይታለች።
በጄኔቭ በተደረሰው ስምምነት መሠረት የቀድሞ በግሪክ የሊቢያ አምባሳደር የነበሩት ሞሐመድ ዩንስ ሜንፊ የፕሬዝደንት ምክር ቤት ኃላፈ ይሆናሉ። በንግድ ሥራቸው ስኬታማ የሆኑት አብዱል ሐሚድ ሞሐመድ ደግሞ የሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚንስትር እንዲሆኑ ተመርጠዋል።
የሽግግር መንግሥቱ ምክር ቤት አባላት ሆነው የተመረጡት ፖለቲከኞች ኃላፊነታቸው በሊቢያ ታኀሣሥ 2021 የሚካሄደውን ምርጫ ማስፈጸም እና በሕዝብ ለሚመረጥ መንግሥት ስልጣን ማስተላለፍ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልዕከተኛ ስቴፈኒ ዊሊያምስ አዲሱ ጠቅላይ ሚንሰትር አዲስ ካቢኔያቸውን አዋቅረው በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ለማጸደቅ 21 ቀናት አላቸው ብለዋል።
ብዙ ካወዛገበው የ2014 ምርጫ ወዲህ በሊቢያ ሁለት ኃያላን ኃይሎች አገሪቷን ሲያምሷት ቆይተዋል። በተለያዩ መንግሥታት የሚደገፉት ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር ጦር ሰፊውን ምስራቅ ሊቢያ ይዞ ይገኛል። በተባበሩት መንግሥት እውቅና የተሰጠው መንግሥት ደግሞ መዲናዋን ትሪፖሊን ተቆጣጥሮ በማስተዳደር ላይ ነው።
ሁለቱም ኃይሎች በሌሎች አገራት ይደገፋሉ። ከሁለቱ ኃይሎች በተጨማሪም ስፍር ቁጥር የሌላቸው ታጣቂ ሚሊሻ ቡድኖች በተለያዩ ፍላጎት ሊቢያን ሰላም ነስተዋት ቆይተዋል።
ጀነራል ሃፍታር ዋነኛ ድጋፍ አድራጊዎች መካከል የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ፣ ግብጽ እና ሩሲያ ተጠቃሾች ናቸው። የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ለጀነራል ሃፍታር ጦር የመሳሪያ ድጋፍ ስለማድረጓ የተመድ ሪፖርቶች አጋልጠዋል። ሩሲያም ከጀነራሉ ጎን የሚዋጉ ቅጥረኛ ወታደሮችን ወደ ሊቢያ ልካለች ተብላ ትታማለች።
በሌላ በኩል በተመድ እውቅና ላለው መንግሥት ጠንካራ ድጋፍ ስታደርግ የቆየችው ቱርክ ነች። አንካራ በይፋ ወታደሮቿን ወደ ትሪፖሊ ልካ በሊቢያ ጠንካራ ልዩነትን መፍጠር ችላለች።