በሲንጋፖር መስጊዶች ሙስሊሞችን ለመግደል ሲያሴር የተገኘ ታዳጊ በቁጥጥር ስር ዋለ

አይስፋህ

የፎቶው ባለመብት, Google

ታትሟል

በሲንጋፖር የ16 አመት ታዳጊ በሁለት መስጊዶች ላይ የሚገኙ ሙስሊሞችን ለመግደል ሲያሴር ደርሸበታለሁ በማለት ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎታል።

ታዳጊው በኒውዚላንድ የደረሰው ክራይስት ቸርች ተብሎ የሚታወቀው ጥቃት ሁለተኛ አመት የተፈፀመበት እለት ላይ ግድያውን ለመፈፀም አቅዶ ነበር ይላል ፖሊስ።

በክራይስት ቸርች ጥቃት አድራሽ ብሬንተን ታራንት የጥፋት ስራ በመነሳሳት ሙስሊሞችን በቢላ ወግቶ ለመግደልና ጥቃቱንና ግድያውን በቀጥታ ለማስተላለፍ አሲሮ እንደነበር ከፖሊስ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ታዳጊው ራሱ ብሬንተን ታራንት በቀጥታ ያስተላለፈውን የሽብርና ግድያ ጥቃት መከታተሉንና "ቪዲዮውን ባየሁት ወቅት ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል" በማለት ተናዟል።

ጥቃት ሊያደርስባቸው ነበሩ የተባሉ መስጊዶች አይሲያፋህና ዩሱፍ የሚባሉ ሲሆኑ ሁለቱም በቤቱ አቅራቢያ እንደሚገኙ ተጠቅሷል።

በአገሪቱ ኢንተርናል ሴኩሪቲ አክት ተብሎ የሚታወቀውና ያለምንም ፍርድ ሂደት ሰዎችን በእስር ማቆየት በሚያስችለው ህግ በቁጥጥር ስር ያለ በእድሜ ትንሹ ነው።

ክራይስት ቸርች በኒውዚላንድ ታሪክ ውስጥ የደረሰ አሰቃቂ የሚባል የጅምላ ጥቃት ነው። ብሬንተን ታራንት ከሁለት አመት በፊት በሁለት መስጊድ የሚገኙ ሙስሊሞች ላይ በከፈተው ተኩስ 51 ሰዎችን ገድሏል። ግለሰቡም የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።

ስሙ ያልተጠቀሰው የ16 አመቱ ሲንጋፖራዊ እምነቱ ፕሮቴስታንት ክርስቲያን እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን "ለእስልምና ባለው ከፍተኛ ጥላቻና ለጥቃትም ካለው አድናቆት ጋር በተያያዘ ነው ለመግደል የተነሳሳው" በማለት የአገሪቷ የውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታውቋል።

እንዲህ በነጭ ፅንፈኞች ቡድን ርዕዮተ አለም ተፅእኖ ስር በመውደቅ የተነሳሳ የመጀመሪያው በቁጥጥር ስር የዋለ ታዳጊ ነው ተብሏል።

የሽብር ጥቃትም ሆነ አሰቃቂ ወንጀሎች በሲንጋፖር የተለመዱ አይደሉም። ታዳጊው ለአንድ ወር ያህል በእስር ላይ ነው።