አደጋ በደረሰበት የኢንዶኔዥያ አውሮፕላን ተሳፋሪ የነበሩት አዲሶቹ ሙሽሮችና ሌሎች

በፖንቲያናካ ሱፓዲኦ አየር ማረፊያ ልዩ የምርመራ ማዕከል ተዘጋጅቷል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በኢንዶኔዥያ ቅዳሜ ዕለት የተከሰከሰው ቦይንግ 737 አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎችና የበረራ ቡድን አባላት ቤተሰቦች የነፍስ አድን ሥራው አንዳች መልካም ዜና ይዞልን ይመጣ ይሆናል በማለት በሃዘን ተሰቅዘው እየተጠባበቁ ነው።

ቅዳሜ ዕለት ከጃካርታ አየር ማረፊያ ከተነሳ ከደቂቃዎች በኋላ ባህር ላይ በተከሰከሰው የመንገደኞች አውሮፕላን ስልሳ ሁለት ሰዎች ተሳፍረው ነበር።

በሕይወት የተረፉ ሰዎችን የማግኘት ተስፋ ያለ አይመስልም።

ምንም እንኳን በአውሮፕላኑ ተሳፍረው የነበሩ ሰዎች ማንነት በይፋ ባይገለፅም፤ ከቤተሰቦቻቸውና ከጓደኞቻቸው መረጃዎች እየወጡ ነው።

የቢቢሲ ኢንዶኔዥያ ጋዜጠኞች ደዊኪ ማርታ እና ዊዲያኒንግሲህ የሚከተሉትን መረጃዎች አጋርተዋል።

"ሸሚዙ ስላልተኮሰለት ቅር ብሎት ነበር"

የስሪዊጃያ ኤስጄ182 አብራሪ የነበረው የእህት ልጅ ፌርዛ ማሃርደሂካ "ሃዘን ላይ ነን። መልካም ነገር እንሰማ ዘንድ እየፀለይን ነው" ብሏል።

የ54 ዓመቱ አብራሪ አፍዋን፣ አውሮፕላኑ የተከሰከሰ ቀን ከቤት የወጣው ተጣድፎ ነበር።

ሸሚዙ ባለመተኮሱም ቅር ብሎት እንደነበር ፌርዛ ያስታውሳል። አብራሪ አፍዋን ሁልጊዜም ሽክና ጽድት ያለ ነው።

የዚያን ቀን ከቤት ሲወጣም ሦስት ልጆቹን ድጋሜ ትቷቸው ሊሄድ ስለሆነ ይቅርታ ጠይቋቸው ነበር።

የስሪዊጃያ ኤስጄ182 አብራሪ

የፎቶው ባለመብት, ENDAH

በሁሉም ኢንዶኔዥያዊያን ተወዳጅ የሆነው አብራሪ አፍዋን፤ በአውሮፓዊያኑ 1987 የንግድ አውሮፕላን አብራሪ ከመሆኑ በፊት የአብራሪነት ሥራውን የጀመረው የጦር አውሮፕላን በማብረር ነበር።

ሃይማኖቱን አክባሪ እንደሆነም ጓደኞቹና ቤተሰቦቹ ይናገራሉ።

በሥራ ቦታም ሆነ በሚኖርበት አካባቢ ሰዎችን ለመርዳት ፍላጎት ያለው ሰው እንደነበርም ፌርዛ ይናገራል።

አብራሪ አፍዋን፤ የማህበራዊ ሚዲያ ገጹ መለያ ፎቶው 'ሱፐርማን' ሲጸልይ የሚያሳይ የካርቱን ምስል ሲሆን "ምንም ያህል ከፍታ ላይ ብትበር፤ ካልፀለይክ በስተቀር ገነት መግባት አትችልም" የሚል ጽሁፍ አለው።

"በጣም መልካም ሰው ነበር፤ ምክር ይሰጠናል፤ በጣም ጠቃሚ ምክር፤ በአካባቢው በጣም የሚታወቅ ሰው ነበር፤ ይበልጥ የሚታወቀው በደግነቱ ነበር" ይላል ፌርዛ ማሃርዲሂካ ስለ አጎቱ ሲናገር።

"በጣም ነው ያዘንኩት፤ ይህ መሆኑን ማመን አልቻልኩም፤ እባካችሁ ለአጎቴ እና ለቤተሰቦቼ ጸልዩልኝ" ሲል ተማጽኗል።

"የልጅ አባት የሆነው ከሳምንት በፊት ነበር"

አፍሪዳ በአውሮፕላኑ ተሳፍሮ የነበረውን የ29 ዓመት ወንድ ልጇን አንጋ ፈርናንዳን በሕይወት እንደምታገኘው ተስፋ አድርጋለች።

" ጃካርታ የሚገኙ ቤተሰቦችም መረጃዎችን እያፈላለጉ ነው፤ እኔም መሄድ እፈልግ ነበር፤ ነገር ግን በወረርሽኙ ሳቢያ ጉዞ ማድረግ አስቸጋሪ ነው" ትላለች በምዕራብ ሱማትራ የምትኖረው አፍሪዳ።

የ29 ዓመቱ አንጋ የልጅ አባት የሆነው ከሳምንት በፊት ነበር።

እርሷ እንደምትለው ባለቤቷ የልጅ አባት መሆኑ የበለጠ ጠንካራ ሰራተኛ እንዲሆን አበረታቶት ነበር።

አንጋ ፍሪዳ

የፎቶው ባለመብት, BBC INDONESIA

አንጋ በእቃ ጫኝ ጀልባ ላይ ነበር የሚሰራው።

"አርብ ምሽት ደውሎልኝ መርከቡ ስለተበላሸ አለቃው መምጣት እንዳለበት እንደነገረውና ወደ ፖንቲያካ ሊሄድ እንደሆነ ነግሮኝ ነበር" ትላለች እናቱ አፍሪዳ።

ብዙ ጊዜ ለሥራ ጉዳይ ወደ ደሴታማዋ ኢንዶኔዥያ አርኪፔላጎ ይሄዳል። ለመጓዝ የሚመርጠው ግን በጀልባ ነበር። አንዳንዴ ነው በአውሮፕላን የሚጓዘው።

እናቱ አፍሪዳ ልጇ ጠንካራ እና ታዛዥ እንደነበር ትናገራለች። " በጣም ትሁትና ከማንኛው ሰው ጋር መግባባት የሚችል ነበር" ትላለች።

በእጇ የልጇን ፎቶግራፍ የያዘችው አፍሪዳ " ሕይወቱ ካለፈ አስክሬኑን ቤት ወስጄ በክብር እንዲያርፍ አደርጋለሁ" ስትልም በተሰበረ ልብ ተናግራለች።

አዲሶቹ ሙሽሮች

በአውሮፕላኑ ተሳፍረው ከነበሩ መንገደኞች መካከል አዲስ ሙሽሮችም ይገኙበታል። ኢህሳን አድህላን እና ፑትሪ ዋህዩኒ። የኢህሳን ታናሽ ወንድም አርዊን አምሩ ለአንድ ድረ ገጽ እንደተናገረው ወንድሙ በረራቸው በመጥፎ የአየር ጠባይ ምክንያት መዘግየቱን ለቤተሰቦቹ ለመናገር ሶኦካርኖ ሃታ አየር ማረፊያ ሳለ ደውሎ ነበር።

ጥንዶቹ ለሰርጋቸው የኢህሳን ዘመዶች ያዘጋጁት ድግስ ላይ ለመገኘት ወደ ካሊማንታን እየተጓዙ ነበር።

ፕሮግራሙ በሳምንቱ ቅዳሜ ቀን ይካሄዳል ተብሎ ነበር የታቀደው። አሁን ላይ ግን ይሆናል ብለው ያላለሙት ገጥሟቸዋል።

ደስታው ወደ ሃዘን ተለውጧል፤ ጭንቀት ወርሷቸዋል።

"ለፕሮግራሙ የተሰባሰቡት ሁሉም ቤተሰቦች ፀሎት ላይ ናቸው" ብሏል አርዊን።

ባልና ሚስት ከአራስ ልጃቸው ጋር

ዩስሪላኒታ ሴት ልጇን፣ የልጇን ባል እና ልጃቸውን ያሳፈረው አውሮፕላን መከስከሱን ስትሰማ ራሷን ስታ ነበር።

ልጃቸው ኢንዳህ ለመውለድ ጃቫ ወደሚገኘው የቤተሰቦቿ ቤት ተጉዛ ነበር። ከዚያም ከባለቤቷ ጋር ፖንቲያንካ ወደ ሚገኘው ቤታቸው እየተጓዙ ነበር ይህ አደጋ የገጠማቸው።

የአገሪቷ መገናኛ ብዙሃን እንዳለው፤ አውሮፕላኑ ከመነሳቱ በፊት አንዳህ የአውሮፕላኑን ክንፍ ፎቶ አንስታ ከባድ ዝናብ እየዘነበ እንደሆነና ቤተሰቦቿ በፀሎታቸው እንዲያስቧት በመግለፅ ፎቶውን በዋትስአፕ መልዕክት ልካ ነበር።

ባለሥልጣናት በፖንቲያናካ ሱፓዲኦ አየር ማረፊያ ልዩ የምርመራ ማዕከል አዘጋጅተዋል። ማዕከሉ የተዘጋጀው የሟቾቹን ማንነት ለመለየት ይረዳ ዘንድ ከቅርብ ዘመዶቻቸው የዘረ መል ቅንጣት ለመውሰድ ነው።

የዘረመል ቅንጣት ናሙና ለመሰብሰብም 51 ባለሙያዎች መሰማራታቸውን ረዳት ኮሚሽነር ያኒ ፐርማና ተናግረዋል።

አሁን የተጎጂ ቤተሰቦች ወደ ቦታው እየሄዱ መሆናቸውን በመግለፅ፤ ሂደቱ ቢያንስ ተጨማሪ ሁለት ቀናትን እንደሚወስድ ይጠበቃል ብለዋል- ኮሚሽነሩ።

ስሪዊጃያ የተባለው አየር መንገድ አውሮፕላን ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 አውሮፕላን ደብዛው የጠፋው ቅዳሜ ዕለት በአገሪቱ ምዕራብ ካሊማንታን ግዛት ወደምትገኘው ፖቲያናክ ወደተባለች ስፍራ በመብረር ላይ ሳለ ነበር።

አውሮፕላኑ ከ130 ሰዎችን የማሳፈር አቅም ቢኖረውም በዚህ በረራው ግን 56 መንገደኞችንና 6 የበረራ ሠራተኞችን ይዞ ነበር ጉዞውን ያደረገው።

የበረራ መከታተያ ድረ ገጽ እንዳለው የአውሮፕላኑ ግንኙነት የተቋረጠው ከ10 ሺህ ጫማ በላይ በሆነ ከፍታ ላይ ከደረሰ ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው።