የኢንዶኔዢያው አውሮፕላን የበረራ መረጃ መመዝገቢያ ሳጥን ያለበት ታወቀ

ታትሟል

ቅዳሜ ዕለት ለመብረር ከጃካርታ አየር ማረፊያ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ባሕር ላይ የወደቀው መንገደኞች አውሮፕላን የበረራ መረጃ መመዝገቢያ ሳጥን (ብላክ ቦክስ) የት እንዳለ መለየታቸውን የአገሪቱ ባለሥልጠናት አስታወቁ።

በአውሮፕላኑ ፍለጋ ላይ ተሰማርተው የነበሩ መርከቦችና የባሕር ኃይል ጠላቂዎች ሳጥኑን ከባሕሩ ውስጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያወጡትም ተናግረዋል።

የአውሮፕላኑ የተለያዩ ክፍሎችና የሰዎች አስከሬንም በፍለጋው መገኘቱ ተገልጿል።

በሚደረገው ፍለጋ ከአደጋው በህይወት የተረፈ ሰው ለማግኘት የሚያስችል ምንም ተስፋ እንደሌለ እየተነገረ ነው።

የኢንዶኔዢያ ባለስልጣናት ከዋና ከተማዋ ጃካርታ ከተነሳ በኋላ የተሰወረው ቦይንግ 737 አውሮፕላን ወድቆበታል ብለው ያመኑትን ቦታ ባሕር ላይ መለየታቸውን ዛሬ ጠዋት ነበር ያስታወቁት።

የስሪዊጃያ አየር መንገድ ንብረትና 62 መንገደኞችን አሳፍሮ ለመጓዝ ከተነሳ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደብዛው የጠፋው አውሮፕላን በአገር ውስጥ በረራ ላይ ነበረ።

ዛሬ ከባሕር ውስጥ የአውሮፕላኑ የበረራ መመዝገቢያ ሳጥን ሳይሆን አይቀርም የተባለ ምልክት በፍለጋ ላይ በተሰማሩ ሠራተኞች ተገኝቷል።

አውሮፕላኑ ወድቆበታል ወደተባለው የባሕሩ ክፍል ከ10 በላይ መርከቦች ከባሕር ኃይል ጠላቂ ባለሙያዎች ጋር መሰማራታቸው ተነግሯል።

"በሁለት ቦታዎች ላይ ከአውሮፕላኑ ጥቁር ሳጥን ውስጥ የተላለፉ ሳይሆኑ የማይቀሩ ምልክቶችን ለይተናል" ሲሉ የኢንዶኔዢያ የአደጋ ጊዜ ፍለጋና ነፍስ የማዳን ተቋም ኃላፊ ባጉስ ፑቱሂቶ ተናግረዋል።

መርማሪዎች የአውሮፕላኑ ናቸው በተባሉ ጎማና ሌሎች ስብርባሪዎች ላይ ምርመራ እያደረጉ ነው።

የጃካርታ ፖሊስ ቃል አቀባይ ዩስሪ ዩኑስ እንደተናገሩት በፍለጋና ነፍስ የማዳን ሥራ ላይ ከተሰማሩ ሠራተኞች ሁለት ሻንጣዎችን መቀበላቸውን አሳውቀዋል።

"አንደኛው ሻንጣ የተሳፋሪዎችን ንብረት የያዘ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ የሰው አካል ያለበት ነው" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ጨምረውም "አስካሁንም የመለየት ሥራ እያከናወንን ነው" ብለዋል።

የፍለጋና ነፍስ የማዳን ሥራው ቅዳሜ ምሽት ላይ እንዲቋረጥ ተደርጎ ዛሬ ዕሁድ ጠዋት ተጀምሯል። በፍለጋው ላይ እንዲያግዙ አራት አውሮፕላኖችም ተሰማርተዋል።

የጠፋው አውሮፕላን ኢትዮጵያ ውስጥ ተከስክሶ ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውና ከበረራ ውጪ እንዲሆን የተደረገው የቦይንግ ማክስ 737 አይነት እንዳልሆነ አየር መንገዱ አሳውቋል።

ምን ተከሰተ?

ከኢንዶኔዢያ ዋና ከተማ ጃካርታ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ግንኙነቱ የተቋረጠውና 62 ሰዎችን አሳፍሮ የነበረው የመንገደኞች አውሮፕላን ባሕር ላይ ሳይከሰከስ እንዳልቀረ ተነገረ።

ስሪዊጃያ የተባለው አየር መንገድ አውሮፕላን ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 አውሮፕላን ደብዛው የጠፋው በአገሪቱ ምዕራብ ካሊማንታን ግዛት ወደምትገኘው ፖቲያናክ ወደተባለች ስፍራ በመብረር ላይ ሳለ መሆኑን ባለስልጣናት ተናግረዋል።

አውሮፕላኑ ከ130 ሰዎችን የማሳፈር አቅም ቢኖረውም በዚህ በረራው ግን 56 መንገደኞችንና 6 የበረራ ሠራተኞችን ይዞ ነበር ጉዞውን ያደረገው።

የበረራ መከታተያ ድረ ገጽ እንዳለው የአውሮፕላኑ ግንኙነት የተቋረጠው ከ10 ሺህ ጫማ በላይ በሆነ ከፍታ ላይ ከደረሰ ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው።

በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ቢያንስ አንድ ፍንዳታ ማየታቸውንና መስማታቸውን ተናግረዋል።

አንድ ዓሳ አስጋሪ ለቢቢሲ የኢንዶኔዢያ አገልግሎት እንደተናገረው የአውሮፕላኑን መውደቅ መመልከቱንና አብሮት ከነበረው መርከበኛ ጋር ወደ ባሕሩ ዳርቻ ለመመለስ መወሰናቸውን ተናግሯል።

"አውሮፕላኑ አንደ መብረቅ ባሕሩ ላይ ወድቆ ውሃው ላይ ነው ፈነዳው" ሲልም ተናግሯል።

የኢንዶኔዢያ ትራንስፖርት ሚኒስቴር አውሮፕላኑን የመፈለግና ነፍስ ማዳን ጥረት እተደረገ መሆኑን ገልጿል።

ኢንዶኔዢያ ውስጥ የአየር መጓጓዣው ዘርፍ ጨምሮ በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ የሚደርሱ አደጋዎች በአንጻራዊነት በተደጋጋሚ ይከሰታል።

ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት የሚጠቀሱት ቁጥሩ የበዛ እንቅስቃሴ መኖር፣ የመሠረተ ልማቶች እርጅናና የልል የደኅንነት ደረጃና ቁጥጥር ናቸው።