ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢንዶኔዢያው አውሮፕላን ባሕር ላይ ሳይወድቅ እንዳልቀረ ተነገረ
ከኢንዶኔዢያ ዋና ከተማ ጃካርታ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ግንኙነቱ የተቋረጠውና 62 ሰዎችን አሳፍሮ የነበረው የመንገደኞች አውሮፕላን ባሕር ላይ ሳይከሰከስ እንዳልቀረ ተነገረ።
ስሪዊጃያ የተባለው አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 አውሮፕላን ደብዛው የጠፋው በአገሪቱ ምዕራብ ካሊማንታን ግዛት ወደምትገኘው ፖቲያናክ ወደተባለች ስፍራ በመብረር ላይ ሳለ መሆኑን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ ከ130 በላይ ሰዎችን የማሳፈር አቅም ቢኖረውም በዚህ በረራው ግን 56 መንገደኞችንና 6 የበረራ ሠራተኞችን ብቻ ይዞ ነበር ጉዞውን ያደረገው።
የበረራ መከታተያ ድረ ገጽ እንዳለው፣ የአውሮፕላኑ ግንኙነት የተቋረጠው ከ10 ሺህ ጫማ በላይ በሆነ ከፍታ ላይ ከደረሰ ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው።
በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ቢያንስ አንድ ፍንዳታ ማየታቸውንና መስማታቸውን ተናግረዋል።
አንድ ዓሳ አስጋሪ ለቢቢሲ የኢንዶኔዢያ አገልግሎት እንደተናገረው የአውሮፕላኑን መውደቅ መመልከቱንና አብሮት ከነበረው መርከበኛ ጋር ወደ ባሕሩ ዳርቻ ለመመለስ መወሰናቸውን ተናግሯል።
"አውሮፕላኑ አንደ መብረቅ ባሕሩ ላይ ወድቆ ውሃው ላይ ነው የፈነዳው" ሲልም ተናግሯል።
"ለእኛ በጣም ቅርብ ነበረ፤ ስብርባሪው የነበርንበትን መርከብ ለጥቂት ሊመታው ነበር።"
የኢንዶኔዢያ ትራንስፖርት ሚኒስቴር አውሮፕላኑን የመፈለግና ነፍስ የማዳን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።
ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የኢንዶኔዢያ ባሕር ኃይል አውሮፕላኑን ለመፈለግ ተሰማርቷል። የባሕር ኃይሉ ባለሥልጣን አብዱል ራሲድ ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት አውሮፕላኑ የወደቀበትን ስፍራ ለይተው መርከቦች ወደ ቦታው መሰማራታቸውን ገልጸዋል።
የአውሮፕላኑ ስብርባሪ ናቸው የተባሉ ነገሮችን የሚያሳዩ ምስሎች በቴሌቪዥንና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየታዩ ነው።
አውሮፕላኑ ከግንኙነት ውጪ ሆኖበታል ከሚባለው ደሴት አቅራቢያ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ለቢቢሲ የኢንዶኔዢያ አገልግሎት እንደተናገሩት ከአውሮፕላኑ የተገኙ ናቸው ያሏቸውን ነገሮች አግኝተዋል።
ስሪዊጃያ የአገር ውስጥ የበረራ አገልግሎት የሚሰጥ አየር መንገድ ሲሆን፣ የደረሰበት ስላልታወቀው አውሮፕላኑ መረጃ በማሰባሰብ ላይ እንደሆነ ገልጿል።
አውሮፕላኑ ከዚህ በፊት እዚያው ኢንዶኔዢያና ኢትዮጵያ ውስጥ አሰቃቂ አደጋ የደረሰባቸው አይነት ቦይንግ 737 ማክስ ሞዴል እንዳልሆነ ተገልጿል።
የመጀመሪያው የ737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ከሁለት ዓመት በፊት የኢንዶኔዢያው ላየን ኤር አየር መንገድ አውሮፕላን ባሕር ላይ በወደቀበት ጊዜ ለ189 ሰዎች ሞት ምክንያት እንደሆነ ይታወሳል።
ኢንዶኔዢያ ውስጥ የአየር መጓጓዣው ዘርፍ ጨምሮ በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ የሚደርሱ አደጋዎች በአንጻራዊነት በተደጋጋሚ ይከሰታል።
ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት የሚጠቀሱት ቁጥሩ የበዛ እንቅስቃሴ መኖር፣ የመሠረተ ልማቶች እርጅናና ልል የደኅንነት ደረጃና ቁጥጥር ናቸው።